Accessibility Settings

color options

monochrome muted color dark

reading tools

isolation ruler

የምርመራ አዘጋገብን በሚመለከት የተለያዩ ትርጓሜዎች ይሰጡ እንጂ፣ አዘጋገቡ በሚያካትታቸው ነጥቦች ዙሪያ ግን የጋዜጠኝነት ባለሞያዎች ልዩነት የላቸውም። ይልቁንም ሥልታዊ፣ ጥልቀት ያለው፣ ያልተቀዳ ጥናትና ዘገባ፣ ብዙ ጊዜ በምስጢር የተያዙ ጉዳዮችን የሚያጋልጥ ነው በሚለው ላይ ይስማማሉ። ሌሎች ደግሞ ተግባራዊነቱ ላይ የሕዝብ የሆኑ መዝገቦችንና መረጃዎችን በከፍተኛ ደረጃ አካትቶ አትኩሮቱ ማኅበራዊ ፍትህና ተጠያቂነት እንደሆነ አጽንዖት ይሰጣሉ።

በዩኔስኮ የታተመ ‹ስቶሪ ቤዝንድ- ኢንኳየሪ› የተሰኘ የምርመራ ጋዜጠኝነት መመሪያ መጽሐፍ፣ የምርመራ ዘገባን እንደሚከተለው ይተረጉመዋል፤ ‹‹የምርመራ ጋዜጠኝነት ኃይል ባለው ሥልጣን ሆነ ተብሎ አልያም በድንገት በእውነታዎች መደበላለቅና ለመረዳት ግልጽ ባልሆኑ ሁኔታዎች የተደበቁ ጉዳዮችን ለሕዝብ መግለጥን ያካትታል። በምስጢር የተያዙ እንዲሁም በግልጽ የሚገኙ ምንጮችንና ሰነዶችን መጠቀምንም ይጠይቃል።››

በተጓዳኝ የ‹ደች- ፍሌሚሽ› የምርመራ ጋዜጠኝነት ማኅበር (VVOJ) የምርመራ ዘገባን በቀላሉ ‹ወሳኝ እና ጥልቀት ያለው ጋዜጠኝነት› ሲል ይተረጉመዋል

አንዳንድ ጋዜጠኞች ሁሉም ዘገባ የምርመራ ዘገባ ነው ብለው ይሞግታሉ። ይህ በእርግጥ እውነትነት አለው። አንዳንድ የምርመራ ዘዴዎችን በሥራቸው የመጨረሻ ሰዓታት ላይ የሚገኙና በአንድ ጉዳይ ላይ አተኩረው የሚሠሩ ጋዜጠኞች ይጠቀሙታል። እንዲሁም የምርመራ ዘገባ ቡድን አባላት አንድን ዘገባ ለመሥራት ባላቸው አጭር ጊዜ ሊጠቀሙት ይችላሉ። ግን የምርመራ ጋዜጠኝነት ከዚህ በእጅጉ ይሰፋል። የጥበባዊ አሠራሮች አንድነት ሲሆን፣ በዘርፉ ብቁ ለመሆንም ዓመታትን የሚጠይቅ ነው።

በምርመራ ጋዜጠኝነት ከፍተኛ ሽልማቶችን ያገኙ ዘገባዎች፣ ሙያው ምን ያህል ከፍተኛ ደረጃ ላይ ያለ ጥናታዊ ምርምርና አዘጋገብ እንደሚፈልግ ማሳያ ናቸው። እነዚህም የተዘረፈ የሕዝብ ገንዘብ፣ ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀም፣ የአካባቢ ብክለት፣ የጤና ዘርፍ ላይ ያሉ አሳፋሪ ጥፋቶችንና መሰል ሌሎች ጉዳዮችን የሚከተሉና ጥልቅና በጥንቃቄ የተመሉ ምርመራዎች ናቸው።

አንዳንዴ ጥልቀት ያለው ዘገባ ወይም የፕሮጀክት ዘገባ እየተባለ የሚጠቀሰው የምርመራ ጋዜጠኝነት ከ‹ሊክ ጆርናሊዝም› ወይም በተለይ የፖለቲካ ሥልጣን ላይ ካሉ ሰዎች የሚገኙ ሰነዶችና ሐሳቦች በመጠቀም ከሚሠራው ሥራ ጋር መቀላቀል ተገቢ አይደለም። በእርግጥ ዴሞክራሲ ብቅ እያለ ባለባቸው አካባቢዎች፣ ትርጉሙ አሻሚ ሊሆን ይችላል። በዚህም መሠረት በድብቅ የወጡ ሰነዶችን ያካተተ ወይም ወሳኝ የሆነ ዘገባ ሁሉ የምርመራ ዘገባ ተብሎ ሊጠራ ይችላል። በተመሳሳይ ወንጀል ወይም ሙስና ላይ ያተኮረ ዘገባ፣ ትንታኔ ወይም ወጣ ያሉ ዕይታዊ ጽሑፎች ጭምር በስህተት የምርመራ ዘገባ ተብለው ሊጠሩ ይችላሉ።

በሙያው አንጋፋ የሆኑ አሠልጣኞች እንደሚሉት፣ ምርጥ የሚባል የምርመራ ጋዜጠኝነት በጥንቃቄ የተመላ ዘዴ፣ ከመጀመሪያ ደረጃ ምንጭ የተገኙ መረጃዎች ላይ መሠረቱን የጣለ፣ መላምት ያለውና ያንንም የሚፈትሽ እንዲሁም ማስረጃዎችን በተደጋጋሚ ማጣራትን የሚያካትት ነው። መዝገበ ቃላቱም ‹ምርመራ› የሚለውን ቃል ‹ሥልታዊ ምርምር› ሲል ይተረጉመዋል። ይህም በአንድ ቀን ወይም በኹለት ቀን ተሠርቶ የሚጠናቀቅ አይደለም፤ ሰፊ ምርመራ ጊዜን ይፈልጋል።

በዘርፉ ለአዳዲስ ዘዴዎች ጥርጊያ የሚሆኑ ነጥቦች አሉ። ለምሳሌ በ1990 ኮምፕዩተሮችን መጠቀም ለመረጃ ትንተና እና ምልከታ ረድቷል። ‹‹የምርመራ ዘገባ አዳዲስ ዘዴዎችንና ነገሮች በአዲስ መንገድ እንዴት ማድረግ እንደሚቻል ያስተምራልና ጠቃሚ ነው።›› ይላሉ፣ ለምርመራ ዘጋቢዎችና ባለሞያዎች ዋና አዘጋጅ ሆነው ለዓመታት ያገለገሉትና በኢሊኖይስ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል መሪ ብራንት ሆስተን። አክለውም አሉ፤ ‹‹እነዛ ዘዴዎች ሲሰርጹ በእለታዊ አዘጋገብ ላይም ይካተታሉ። እናም በምርመራ ጋዜጠኝነት መነሻነት በጠቅላላ የሙያውን አጥር እያሰፋን እንሄዳለን›› ብለዋል።


ከዓለማቀፉ የምርመራ ጋዜጠኝነት የድጋፍ ሥልቶች ተቀንጭቦ የተወሰደ፤ በዴቪድ ካፕላን፣ የዓለማቀፍ የሚድያ ድጋፍ ሰጪ ማእከል፤ 2013። ካፕላን የዓለማቀፍ የምርመራ ጋዜጠኝነት ኔትወርክ ዋና ዳይሬክተር ናቸው፣ ኔትወርኩ የ184 ለትርፍ ያልተቋቋሙ ማኅበራት ስብስብ ሲሆን በ77 አገራት የምርመራ ዘገባን ለመደገፍ የሚሠራ ነው።


ተጨማሪ ዕይታዎች 

የምርመራ ጋዜጠኝነት ምንድን ነው፤ የ2010 የግሎባል ሚድያ ፕሮግራሞች ፕሮጀክት የሆነው የምርመራ ጋዜጠኝነት መመሪያ የመጀመሪያው ምዕራፍ።