Accessibility Settings

color options

monochrome muted color dark

reading tools

isolation ruler

አዲስ የተከሰተው የኮሮና ቫይረስ የዓለማችን ትልቁ ዜና ሆኖ ቀጥሏል። እንደ ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ እስከ አሁን የኮሮና ቫይረስ ከ167 በላይ የዓለም አገራትን አዳርሶ፣ 11 ሺሕ በላይ ሰዎችን ገድሏል። ከ286 ሺሕ በላይ ሰዎች ደግሞ በበሽታው ተይዘዋል።

የዓለም የጤና ድርጅት በ2001 ነበር የአሳማ ጉንፋን ወይም ስዋይን ፍሉን የመጀመሪያው ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ብሎ ያወጀው። ኮቪድ19 ስድስተኛው ዓለም አቀፍ የኅብረተሰብ ጤና አደጋ ተብሎ የታወጀ ሲሆን፣ ዓለማቀፍ ወረርሺኝ እስከመሆንም ደርሷል። የቫይረሱ ስርጭት ከዓለማችን ኢኮኖሚ ላይ ቢሊዮኖችን ሙልጭ አድርጎ የወሰደ ከመሆኑ በላይ፣ እንደ ብሉምበርግ ዘገባ ከሆነ በሂደት ከዓለማቀፉ ኢኮኖሚ ሦስት ትሪሊዮን ዶላር የሚጠጋ ሃብት ሊያሳጣት ይችላል።

ከእነዚህ ቁጥሮች እና ግምቶች ባሻገር ኮቪድ19 ምን ያህል ይሰራጭ ይሆናል? እንዲሁም ይዞት የሚመጣው መዘዝ የት ይደርሳል? የሚለውን መገመት ግን አሁንም አስቸጋሪ ነው። ነገሮች እንዲህ ባልጠሩበት ሁኔታ፣ በዓለም ዙሪያ ያሉ ጋዜጠኞች ወረርሽኞችን በሚዘግቡበት ወቅት የሐሰት መረጃዎችን አጥርቶ ትክክለኛውን ለመያዝ ብሎም በመስክ ላይ ያለውን የጤና አደጋ ጨምሮ ለብዙ ችግሮች ይጋለጣሉ። አላስፈለጊ ጭንቀትን ላለማባባስ የሚያደርጉት ጥረትም ሌላው ፈተና ነው።

ታዲያ በእንዲህ አይነት አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ጋዜጠኞችን ለማገዝ ይረዳ ዘንድ የዓለም ዐቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ትስስር (GIJN) አባል ሚራጅ ቾውዱሪ ከተለያዩ የጋዜጠኞች ማኅበራት፣ ልምድ ካካበቱ ጋዜጠኞች እና ከባለሞያዎች ግብአቶችን አሰባስቧል። ይህ ብቻ ሳይሆን ሃብት በማሰባሰብ ዘገባዎችን ለማገዝ ጥረት የምናደርግ ሲሆን ይህም የዘገባ መመሪያዎችን በተለያዩ ቋንቋዎች በማዘጋጀት በተለያዩ የማህበራዊ ድህረገፆቻችን ማቅረብን ያጠቃልላል።

ለጊዜውም የባንግላዲሽ የኮቪድ19 አዘጋገብ መመሪያችን፣ በቻይና ትስስራችን ያጋጀው ሕዝቡ ለኮቪድ19 ያለው እይታ ላይ ያተኮረውን ዘገባ እንዲሁም የተላላፊ በሽታዎች ባለሞያ የሆኑት እና በሳርስ እና በፖሊዮ ላይ መጽሐፍ የጻፉት ቶማስ አብራሃም ያዘጋጁት ምክሮችን ለምርመራ ጋዜጠኞች ተዘጋጅተዋል።

በኃላፊነት መዘገብ

በካርዲፍ ዩኒቨረሲቲ የጋዜጠኝነት ፕሮፌሰሯ ካሪን ዋህል-ጆርግሰን በቅርቡ ባሳተሙት ምርምራቸው፣ በዓለም ላይ ከፍተኛ አንባቢ ያላቸውን 100 ጋዜጦችን በመምረጥ ፍርሃት በኮቪድ19 አዘጋገብ ላይ የነበረውን ሚና ገምግመዋል። ‹‹እነዚህ ዘገባዎች ብዙ ጊዜ አስፈሪ ቃላትን የሚጠቀሙ ሲሆን፣ 50ዎቹ መጽሔቶች ‹ገዳይ ቫይረስ› የሚለውን ሐረግ ተጠቅመዋል›› ሲሉ ፕሮፌሰሯ ያስረዳሉ። ‹‹ከዘጠኝ ዘገባዎች ውስጥም አንዱ ‹ፍራቻ› የሚለውን ቃል ወይም ሌላ ተመሳሳይ አስደንጋጭ ቃል ይጠቀማል›› ሲሉ በነኢማን ላብ ጽሑፋቸው ላይ ያስረዳሉ።

በዚህ ወቅት ድንጋጤን በመቀነስ ጥልቅ እና ሚዛናዊ ዘገባን እንዴት ማቅረብ እንችላለን ለሚለው ጥያቄ በኮቪድ19 ላይ በየቀኑ የሚታተም በራሪ ጽሑፍ በማተም ላይ የሚገኘው የፖይንተር ባልደረባ የሆኑት አል ቶምፕኪንስ፣ መፍትሄው በኃላፊነት መዘገብ ነው ይላሉ።

ምክሮቹ ባጭሩ

 1. ጋዜጠኞች ‹ግምታዊ ፅንሰ ሐሳቦችን ማካተት ማቆም አለባቸው። ለምሳሌ ‹ገዳይ በሽታ› የሚለውን፤
 2. ፎቶዎችን ስንመርጥ የተሳሳተ መረጃ እንዳናሰራጭ በጥንቃቄ ማስተዋል፤
 3. የመከለከል እርምጃዎችን በአግባቡ በማብራራት ዘገባችንን በጣም አስፈሪ እንዳይሆኑ ማድረግ፤
 4. በቁጥር ላይ የተመሠረቱ ዘገባዎች በሰዎች ታሪክ ላይ ከተመሰረቱ ዘገባዎች ይልቅ ፍርሃትን ይቀንሳሉ፤
 5. ትኩረት ለመሳብ ሲባል አላስፈላጊ ርዕሶችን ከመጠቀም ይልቅ በጥበብ የታገዘ አቀራረብ መምረጥ፤

በሌላ የፖይነተር ጽሑፍ ላይ, ቶም እውነታውን በማግኘት ላይ እንጂ ንግግሮችን በማግኘት ላይ አንዳናተኩር አፅንኦት ሰጥቶ ይመክራል።

‹‹ይሄ የሳይንስ ዘገባ እንጂ የፖለቲካ አይደለም›› የሚለው ቶም ‹‹በእርግጥም ፖለቲካ አስፈላጊ ነው። ነገር ግን ስለ ኮቪድ19 የፖለቲካ አቋም ካላቸው ምንጮች በመጠንቀቅ በጤና ባለሞያዎች ላይ መመስረት ያስፈልጋል›› ሲል ያክላል።

ሥያሜ መስጠት

ኮቪድ19 ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ ዘጋቢዎች የተለያየ ሥም በመጠቀም ቫይረሱን ሲጠሩት ሰንብተዋል። ለምሳሌ ‹‹አዲሱ የኮሮና ቫይረስ፤ ኖቭል ኮሮና ቫይረስ፣ የኮሮና ቫይረስ›› የሚሉት ይገኙበታል። ‹‹ይሄኛው የኮሮና ቫይረስ ከዚህ ቀደም ተከስተው የየራሳቸውን አይነት በሽታ እና ወረርሺኝ ፈጥረው ከነበሩት ቫይረሶች የተለየ ነው። እያንዳንዱ የኮሮና ቫይረስ ክስተት የራሱ የሆነ ሥም የሚወጣለት ሲሆን፣ በተከሰበት ወቅት ሁሉም አዲስ (ኖቭል) ነበር›› ሲሉ ሜሪል ፕርል ማን በቅርቡ በኮሎምቢያ ጆርናሊዝም ሪቪው ላይ ባሳተሙት ጽሑፋቸው ላይ ያትታሉ።

ስለ ሥሞች በዝርዝር ማወቅ የሚፈልጉ ከሆነ የዓለም ጤና ድርጅት ለምን ቫይረሶች የተለያየ ሥም እንደሚሰጣቸው የሚያብራራበትን ጽሑፍ ይመልከቱ።

አዲስ የተቀሰቀሰ ወረርሺኝን እንዴት መሰየም ይቻላል? ሲኤንኤን አዲስ የተቀሰቀሰውን የኮሮና ቫይረስ ዓለም ዐቀፍ ወረርሺኝ እያለ ይጠራዋል፤ ምንም እንኳን ሲኤንኤን ይህንን ቃል መጠቀም በጀመረበት ወቅት የዓለም የጤና ድርጀት በሽታውን ዓለም ዐቀፍ ወረርሺኝ ብሎ ባይሰይመውም።

የሲኤን ኤን አርታኢዎች ግን ይህንን ለምን እንደሚጠቀሙ ያብራራሉ። (የአርታኢው ማስታወሻ፡ የዓለም የጤና ድርጅት አሁን በሽታውን ዓለም ዐቀፍ ወረርሺኝ ብሎ ሰይሞታል።)

ቃላት ትልቅ ዋጋ አላቸው። እንደ አሶሺየትድ ፕሬስ የአጻጻፍ ስልት መመሪያ መጽሐፍ ‹‹ወረርሺኝ ማለት በተወሰነ ሕዝብ ወይም አካባቢ በፍጥነት የሚሰራጭ በሽታ ማለት ሲሆን፣ ዓለም ዐቀፍ ወረርሺኝ ማለት ደግሞ ስርጭቱ በተወሰነ የዓለም ክፍል ከመወሰን ይልቅ በመላው ዓለም ሲሆን ነው። ነገር ግን የኅብረተሰብ ጤና ባለሞያዎችን ብያኔ በመጠበቅ ይህንን ቃላትን እንድንጠቀም ይመክራሉ። ተጨማሪ ምክሮችን ከአሶሺየትድ ፕሬስ የአጻጻፍ ስልት መመሪያ መጽሐፍ ላይ ይመልከቱ

ራሳችንን መጠበቅ

ዓለማቀፍ ወረርሽ በሚከሰትበት ወቅት ጋዜጠኞች ራሳቸውን አግልለው ዘገባ ማካሄድ አለመቻላቸው እሙን ነው። ምንም እንኳን በበሽታው የመያዝ አደጋ ቢኖርም ወደ መስክ ወጥቶ መዘገብ ግን አይቀሬ በመሆኑ በበሽታው የመጠቃት እድል ይኖራል። የጋዜጠኞችን ደኅንነት ለመጠበቅ የተቋቋመው ሲፒጄ፣ በኮቪድ19 ላይ ዘገባ ለሚያዘጋጁ ጋዜጠኞች የደኅንነት መጠበቂያ ምክሮች እና መመሪዎች አውጥቷል። ይህም የቅድመ ዳሰሳ ዝግጅቶች፣ በሽታው በተስፋፋበቸው አካባቢዎች በበሽታው የመያዝ እድልን መቀነስ፣ የጉዞ እቅድ አወጣጥ እንዲሁም ከዘገባ በኋላ ሊወሰዱ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች ያጠቃለለ ነው።

ከእነዚህ ምክሮችም አንኳሮቹ እና ሊዘነጉ የማይገባቸው መካከል በአጭሩ፤

 • 1/ እንደ ሆስፒታል ያሉ በቫይረሱ የተበከሉ አካባቢዎች ላይ ዘገባውን የምንሠራ ከሆነ የእጅ ጓንት መጠቀም ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪም ሙሉ ሰውነትን ለመሸፈን የሚያገለግሉ የፕላስቲክ አልባሳት፣ ሙሉ ፊትን መሸፈኛ ማስክ እና ሌሎች የሕክምና ባለሞያዎች የሚጠቀሙባቸውን የጥንቃቄ ቁሳቁሶችን መጠቀም ሊያስፈልግ ይችላል።
 • 2/ ትኩስ ስጋ ወይም አሳ የሚሸጥባቸውን የገበያ ቦታዎች ወይም በሽታው የተስፋፋባቸውን የግብርና ቦታዎች አይጎብኙ። በተመሳሳይም ሕይወት ካላቸው ወይም ሕይወት ከሌላቸው እንስሳት ጋር ንክኪ እንዳይኖር ጥንቃቄ ያድርጉ። እንስሳት የሚፀዳዱባቸው ቦታዎችን ላለመርገጥ ወይም ላለመንካት ጥንቃቄ ያድርጉ።
 • 3/ በጤና ጣቢያዎች፣ በገበያዎች እና በግብርና ቦታዎች አካባቢ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ከሆነ ማንኛውንም ቁሳቁስ መሬት ላይ ከማስቀመጥ ይቆጠቡ። ቁሳቁሶችዎትን ሁሌም በፀረ-ባክቴሪያ ማፅዳትዎትን አይዘንጉ። በተለይም እንደ ሜልሴፕቶል ያሉ ማፅጃዎችን ይጠቀሙ።
 • 4/ ከእንስሳት ጋር ንክኪ ባለበት ወቅት፣ ገበያ ወይም የግብርና ቦታ በአቅራቢያዎ ካለ፣ ምንም አይነት ምግብ ወይም መጠጥ አይጠቀሙ።
 • 5/ ቫይረሱ ወደተስፋፋበት አካባቢ ከመግባትቆ በፊት፣ በቦታው ላይ ሥራዎትን እያከናወኑ ወይም ሥራዎትን አጠናቀው ሲወጡ ሁሌም እጅዎትን በሞቀ ውሃ እና በሳሙና በደንብ ይታጠቡ።

ባለሞያዎቹ

ፎቶ፡ ፒክሳቤይ

ሁሌም ኮቪድ19ኝን በተመለከተ ወቅታዊ መረጃን ለማግኘት የዓለም ጤና ድርጅትን፣ መሠረቱን በአሜሪካ ያደረገውን የሲዲሲን እና የዩናይትድ ኪንግደሙን የኅብረተሰብ ጤና ድረ-ገፆች ቢመለከቱ መልካም ነው። በተጨማሪም የጆን ሆፕኪኒስ ዩኒቨርሲቲ እና ሜዲሲን የኮቪድ19 ካርታ፣ የኮሮና ቫይረስ የመረጃ ማእከሉን እና በፍጥነት የሚዘጋጁትን የበራሪ ወረቀቶች መረጃን መመልከት ጠቃሚ ነው። በተጨማሪም በሚኖሩበት አካባቢ በሽታውን በተመለከተ ሥልጣን ያለውን የመንግሥት አካል በቅርበት ይከታተሉ።

የጋዜጠኞች ጠቃሚ የመሣሪያ ሳጥን፣ በፕሮፌሽናል ጋዜጠኞች ማኅበረሰብ የተዘጋጀ ሲሆን፣ እንዲህ ቀንጭበን እናቀርበዋለን

ለተጨማሪ መረጃ በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ መሰረቱን ያደረገው ናሽናል ፕረስ ክለብ ያዘጋጀውን የቪዲዮ መግለጫ፣ ወይም የሳውዝ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ አኔበርግ የጤና ጋዜጠኝነት ማእክል ያዘጋጀውን ተመሳሳይ የቪዲዮ መግለጫ ይመልከቱ።

በኮቪድ19 ላይ የጤና ባለሞያዎችን ማግኘት ከባድ እንደሚሆን ይገመታል። ቫይረሱ ገና አዲስ እና የማይገመት ከመሆኑ በሻገር በኮቪድ19 ላይ ምርምር ያደረጉ ባለሞያዎችን ወይም ሐኪሞችን ማግኘትም እንዲሁ በቀላሉ የሚሳካ አይደለም።

ዊሊያም ሃንጌ በሃርቫርድ ቲኤች ቻን የኅብረተሰብ ጤና ትምህርት ቤት የኢፒዲሞሎጂ ተባባሪ ፕሮፌሰር ናቸው። ባለሞያዎችን በምንመርጥበት ወቅት ልንጠቅምበት የሚገባንን አምስት ምክሮችን ከግምት ውስጥ ይክተቱ ይላሉ።

ምክሮቹ በአጭሩ

 1. ባለሞያዎችን በጥንቃቄ ይምረጡ። በአንድ ሳይንሳዊ ግኝት ዙሪያ የኖቤል ሽልማትን የወሰደ ሰው በሁሉም ሳይንሳዊ ጥናቶች ላይ ባለሞያ አያደርገውም። በአንድ የትምህርት ዘርፍ ፒኤች ዲ መያዝ ወይም በትልቅ የሕክምና ትምህርት ቤት ማስተማርም እንደዚሁ በሁሉም የጤና ጉዳዮች ላይ ባለሞያ አያደርግም።
 2. እውነት ነው ተብሎ የሚታወቀውን፣ የሚታመነውን እንዲሁም ግምቶችን እና የግል አስተያየቶችን መለየት ያስፈልጋል።
 3. ገና ያልታተሙ የጥናት ውጤቶች ወይም ቅድመ ሪፖርቶችን በምንጠቀምበት ወቅት ሁሌም ይህንን የሚገልፅ ማሳሰቢያዎችን መጠቀም ያስፈልጋል።
 4. ሁሌም አዳዲስ ጽንሰ ሐሳቦችን በምናገኝ ጊዜ ጉዳዩ ለዜና መብቃት አለመብቃቱን፣ ምሁራን እንዲመዝኑልን ማድረግ የተዛቡ መረጃዎችን ለመከላከል ያግዛል። መገናኛ ብዙኀን የውጪ ጸሐፊዎቻቸው ወይም ተባባሪ ፕሮግራም አዘጋጆቻቸው የሚጠቀሙትን መረጃዎች ትክክለኛነት ማጣራት በእንዲህ ዓይነት ወቅት ላይ ከፍተኛ ሚና አለው።
 5. የሳይንስ ዘገባዎችን በመሥራት ልምድ ያካበቱ መገናኛ ብዙኀንን የዘገባ ውጤቶች ይመልከቱ።

የሌሎች ጋዜጠኞች ምክሮች

ዓለም ዐቀፉ የምርመራ ጋዜጠኝነት ትስስር ከቀደምት የጤና ጋዜጠኛ፣ የተላላፊ በሽታዎች ባለሞያ እና የዓለም ዐቀፍ የጤና ደኅንነት ባለሞያው ቶማስ አብርሃም፣ ጋር ካደረገው ቃለ ምልልስ ላይ የተወሰደውን ይህንን ምክር ይመልከቱ። ቶማስ ‹‹የ ትዌንቲ ፈርስት ሴንቸር ፕሌጅ፡ ዘ-ስቶሪ ኦፍ ሳርስ›› የተሰኘውን በሳርስ ላይ የተዘጋጀው እና ‹‹ፖሊዮ፡ ዘ ኦዲሲ ኦፍ ኢራዲኬሽን›› የተሰኘውን በፖሊዮ ላይ የተዘጋጁት መጽሐፍት ደራሲ ናቸው።

በ13 ዓመቷ በሆንግ ኮንግ በሳርስ በሽታ ተይዛ የነበረችው እና ከበሽታው ከተረፈች በኋላም ሳርስ እና ኢቦላ ላይ ቀዳሚ ዘጋቢ ሆና ስታገለግል የነበረቸው ካሮላይን ቼን፣ በፕሮፑብሊካ ላይ የጤና ነክ ጉዳዮች ጸሐፊ ነች። በኮቪድ19 ላይ ባዘጋጀችው በዚህ ጽሑፏ ላይም ኮቪድ19ኝ በምንዘግብበት ወቅት ልንጠይቃቸው የሚገባቡ ጥያቄዎች ምንድን ናቸው የሚለውን ታስረዳለች።

ዘገባዎቻችን በግምት፣ በትንበያዎች እና በጣም በሚቀያያር መረጃ ላይ ቢመሰረቱም እንዴት ትክከለኛ ሆነው መቀጠል ይችላሉ የሚለውን እና ከምንም በላይ ግን እንዴት ራሳችንን ጠብቀን መዘገብ እንችላለን የሚለውን ታስረዳለች።

በጤና ጉዳይ ላይ ከ20 ዓመታት በላይ ልምድ ያካበተው ጆን ፖፕ ደግሞ ስዋይን ፍሉን በመዘገብ ወቅት ከግምት ውስጥ ልንከታቸው የሚገቡ 11 ምክሮችን ሲል አስነብቧል። ይህ ጽሑፍ ያካተታቸው ምክሮች ለኮቪድ19ኝም ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ። ምክሮቹም መሰረታዊ የሆኑ መረጃዎችን ይዞ መነሳት፣ በሽታውን በካርታ አስደግፎ ማዘጋጀት እና መረዳት፣ ነገሮችን በአጭር እና በቀላሉ ማስቀመጥ፣ ቅድመ መከላከል ላይ ማተኮር እና የምንጠቀማቸው ቃላት ላይ በትኩረት እና በጥንቃቄ መሥራት የሚሉ ናቸው።

የዓለማቀፉ የጋዜጠኞች ትስስር አይጄኔት ያዘጋጀው ኮቪድ19ኝን በምንዘግብበት ወቅት መተግበር ያለባቸው ጠቃሚ ምክሮች እንዲህ በአጭሩ ቀርበዋል፤

 • 1/ አካባቢውን እና በመሬት ላይ ያለውን ሁኔታ በጥሞና በማስተዋል ከዘገባችን ጋር አጣጥሞ መተርጎም ያስፈልጋል፤
 • 2/ ሁኔታውን በመዘገብ እንጂ ትንተና በመስጠት ላይ አለማተኮር፤
 • 3/ ለምንሰጣቸው ርዕሶች ትኩረት መስጠት፤
 • 4/ ሁሉም ቁጥሮች ትክክለኛ ያለመሆናቸውን ማስተዋል፤
 • 5/ ዘረኛ የሆኑ የዘገባ ርእሶችን መቀነስ፤
 • 6/ በተቻለ መጠን የተለያዩ እና ብዙ ሰዎችን ለማነጋገር መሞከር፤
 • 7/ ባለሞያዎችን ቃለመጠይቅ የማድረጊያ ዘዴዎችን በደንብ ማጤን፤
 • 8/ በጣም አስደማሚ አይደሉም በሚል አንዳንድ ዜናዎችን ላይ አለመዘናጋት
 • 9/ ለዘገባዎች ገደብ ማስቀመጥ። አንደንዴ አርታኢዎችን አይሆንም ማለት ይልመዱ፤
 • 10/ ሁኔታዎች በሚረጋጉበት ወቅትም ዘገባዎች መሥራትዎን ይቀጥሉ፣ አያቋርጡ፤

የዓለም የጤና ድርጅት ጋዜጠኞችን ምሮ ሁሉም ሰው ሊጠቀምበት የሚችል አሉባልታ እና የተሳሳቱ መረጃዎችን ለማረጋገጥ የሚረዱ ምስሎችን ያዘጋጃል። ፎቶ፡ ዓለም የጤና ድርጅት

ስለ ኮቪድ19 የሚወጡ መረጃዎችን ማረጋገጥ

የካቲት 4/2012 በተካሄደው የሙኒኩ የደኅንነት ጉባኤ ላይ የተሳተፉት የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ‹‹ከበሸታው ጋር ብቻ ሳይሆን ከመረጃ ወረርሽኝ ጋርም ነው እየታገልን ያለነው›› ማለታቸው ይታወሳል።

በዚህ የተዛቡ እና የሐሰት መረጃዎች ዘመን የኢንተርኔት አፈታሪኮች እና የሴራ ትንተናዎች ከመፈልፈላቸው ባሻገር ጋዜጠኞችም ቻይና ውስጥ የተመረቱ ቁሳቁሶች መጠቀም የኮሮና ቫይረስን ሊያስተላልፉ ይችላሉ፣ ኮቪድ19 በሳይንቲስቶች የተፈበረከ ነው ወይም ከአንድ የተወሰነ ላብራቶሪ የወጣ ነው እንደሚሉት አይነት የተጭበረበረ መረጃዎችን ሊያሰራጩ ይችላሉ።

በቀውስ እና በወረርሺኝ ግዜ ካርታዎች ራሱ ሀሰት ሊሆኑ ይችላሉ በፈርስት ድራፍት የተዘጋጀ

ፖይንተር በአሜሪካ፣ ሕንድ፣ ጋና እና ኢንዶኔዢያን ጨምሮ ቢያንስ በአምስት አገራት የሚኖሩ ሕዝበች ‹‹የቻይና መንግሥት ከአንድ ዓመት በፊት የአገሪቱን ጠቅላይ ፍርድ ቤት 20 ሺሕ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች እንዲገደሉ ፈቃድ እንዲሰጠው ጠይቋል›› የሚለውን ዜና ተመልክተዋል ወይም አንብበዋል ሲል በቅርቡ ባሳተመው ጽሑፉ ላይ አስነብቧል

የተጭበረበሩ እና የሐሰት መረጃዎችን ለማረጋገጥ ሲፈልጉ ከ39 አገራት የተወጣጡ 90 የመረጃ አረጋጋጮችን ባጠቃለለው ዓለማቀፉ የመረጃ አረጋጋጭ ትስስር የተሠራውን እና በአሁኑ ወቅት እንደ ሱናሚ የሆነውን የሐሰት መረጃን ለመዋጋት የሠሩትን ሥራ መመልከት ጠቃሚ ነው።

በየካቲት ወር መጨረሻ #CoronaVirusFacts/ #DatosCoronaVirus የተባሉት ትብብሮች በጋራ የተለያዩ መረጃዎችን አረጋግጠዋል። ፌብሩዋሪ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የኮሮና ቫይረስ የመረጃ አረጋጋጭ ትብብር 558 መረጃዎችን በበሽታው ዙሪያ አረጋግጧል። የዓለም የጤና ድርጅትም ኮሮና ቫይረስን በተለመከተ የሚፈበረኩ የፈጠራ ወሬዎችን የሚያስተባብለበት ‹‹ሚዝ በስተርስ›› የተሰኘ በበሽታው ዙሪያ ያሉ አሉባልታዎችን እና የሚያስተባብልበትን ገፅ ከፍቷል።ይህ ገፅ ለጋዜጠኞች እንዲሁም ለማንኛውም ሰው ጥቅም ላይ ሊውሉ የሚችሉ ምስሎችንም የያዘ ነው።

አጃንስ ፍራንስ ፕሬስም ተመሳሳይ ‹‹በኮሮና ቫይረሱ ዙሪያ ያሉ አፈታሪኮችን ማረጋጋጫ›› የተሰኘ ተመሳሳይ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። ፈርስት ድራፍት የተሰኘው እና ለትርፍ ያልተቋቋመው የሀሰት ምጃን በማረጋጋጥ የሚታወቀው ድህረ ገፅን መጎብኘት በጣም ጠቃሚ ነው። ድህረ ገፁ በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ያሉ የተሳሳቱ መረጃዎችን መቀነስን በተመለከተ በቅርቡ ባዘጋጀው ፅሁፉ እና ይዘቶቻችንን በፍጥነት የምናረጋግጥበት ዘዴዎች ላይ የተዘጋጁት ሁለት ፅሁፎችን ማንበብ ይመከራል።

በአለማችን ላይ ቁጥራቸው ቀላል የማይባ መገናኛ ብዙሃን የመረጃ አራጋጋጭ ቡድን ወይም ግለሰብ የላቸውም። ይህ በሚሆንበት ግዜ እና የጠራ ወሬዎች ወይም አጠራራጣሪ መረጃዎች በሚያጋጥሙ ግዜ በአገር ውስጥ በይም በአሃጉራችሁ ውስጥ ለሚገኙ ጠንካራ እ ታማኝ የእውነታ አረጋጋጮች እርዳታ ጠይቁ። ባብዛኛው እነዚህ የመረጃ አጋጋጮች በማህበራዊ ሚዲያዎቻቸው ላይ በቀላሉ የሚገኙ እና አንዲህ ያሉ ጥቆማዎችንም በፈቃደኝት ይቀበላሉ።

በህመሙ ከተጠቁ ሰዎች እና ከጭንቀት ጋር እንዴት እንጋፈጥ

ለዘጋባዎቻችን በምንዘጋጅበት ወቅት ችግሩን መግለፅ የሚችሉ የሰዎችን ታሪኮችን ማካተት፣ የሰዎችን መኖያ ቤት ወይም የስራ ቦታ መመልከት አንዲሁም ከባድ ጥያቄዎችን መጠየቅ ግዴታ ይሆናል። እንዲህ ባለ ዓለምአፍ ወረርሺኝ ወቅት ሰዎች መደናገጣቸው ደግሞ የማቀር ሲሆን በበሽታው የተጠቁ ሰዎችም ራሳቸውን ይፋ ማውጣት እና ስለ ህመማቸው መናገር ላይፈልጉም ይችላሉ። ይቅር እና ስለ ግለሰቡ ማንነት ስለሚኖርበት አካባቢ መናገር በራሱ ለሚኖርበት ማህበረሰብ ሽብር ሊፈጥር እና የህመምተኛውን ቤተሰብም ደህንነት አደጋ ውስጥ ሊከተው ይችላል።

የዳርት ሴንተር ፎር ጆርናሊዝም ኤንድ ትራውማ ማእከል ታዲያ ይህንን ለመፍታት ኮቪድ19ኝ በምንዘግበበት ወቅት ልንጠቀምባቸው የምንችላቸውን ጠቃሚ መረጃዎች አዘጋጅቷል። ይህም ጠቃሚ ምክሮችን፣ የተመረጡ ልምዶችን እና መመሪያዎችን ያጠቃለለ ነው።

በተጨማሪም የበሽታውን ተጠቂዎች፣ ከበሽታው የተረፉ ሰዎችን እንዴት ቃለ መጠይቅ እናድርግ የሚለውን እና ለከፍተኛ ጭንቀት ከተጋለጡ ባልደረቦቻችን ጋር እንዴት ተግባብተን እንስራ የሚለውንም ከባለሞያ የተለገሱ ምክሮችን አካቷል። በተጨማሪም የጤና ጋዜጠኝነት ማእከል ያዘጋጀው ፅሁፍ ከአደጋ የተረፉ ሰዎችን እንዴት ቃለ መጠይቅ ማድረግ እንደምንችልም ማስተማሪያዎችን የያዘ ነው።

ከእነዚህ ጠቃሚ ምሮች መካከል ጥቂቶቹ

 • 1/ የተጠቂዎችን ክብር ላቅ ባለ ሁኔታ መጠበቅ እና ራሱ ተጠቂው ታሪኩን ለመናር እስኪጋብዝ መጠበቅ
 • 2/ የቃለ መጠየቁን ሰአት እና የቃለ መጠይቁን ሁኔታ ራሱ ተጠቂው በሚመራው ወቅት ይሁን እንጂ ጋዜጠኛው በሚስማማው ሰአት ባይሆን ይመረጣል፣ በዚህ ሰአት የስነ ልቦና ባለሞያዎችን ይዞ ቃለ መጠይቁን ማካሄድ የበለጠ ውጤታማ ያደርጋል
 • 3/ ግልፅ ሁኑ፣ የተጠቂወን ማንነት የምትዘግቡበት አግባብ ላይ በግልጽ በማስረዳት እና በእውቀት ላይ የተመሰረተ ፈቃድ ማግኘት አግባብ ነው።
 • 4/ ከዘገባችሁ በፊት ሰብአዊነትን አስድሙ። የተጠቂውን ደህንነት ቀዳሚ ዘገባችሁን ደግሞ ተከታይ አድርጉ።
 • 5/ ከባድ ትያቄዎች ቀድማችሁ በማቅረብ ተጠቂውን አታስጨንቁ። ትከረት ስጡ አንዲሁም ባግባቡ አዳምጡ።
 • 6/ የስሜት ቀውስ ካጋጠመው ተጠቂ ጋር ተደጋጋሚ ቆይታ ማድረግ ጋዜጠኛውን ራሱ ላይ ጫና ሊያሳድር እንደሚችል ቀድሞ ግምት ውስት መክተት ያስፈልጋል።

የዳርት ማእከል የመጨመረሻው ምክር ግን ሁላችንም ልብ ልንለው የሚገባ ነው

‹‹ራሳችሁንም ጠብቁ››


ሚራጅ አህመድ ቾውዱሪ የዓለም አቀፉ የምርመራ ጋዜጠኞች ትስስር የባንግላዲሽ አርታኢ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪም የመገናኛ ብዙሃንን እና የሲቪል ማህበረሰቡን አቅም ለማጎልበት የሚሰራውን እና በባንግላዲሽ የትስስሩ አባል የሆነውን የኤም አር ዲ ኣይን ፕሮግራሞች እና የግንኙነት ስራዎችን ይከታተላሉ። በተለይም በብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ጋዜጠኝነት የ14 አመት ልምድ አላቸው።

Republish our articles for free, online or in print, under a Creative Commons license.

Republish this article


Material from GIJN’s website is generally available for republication under a Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International license. Images usually are published under a different license, so we advise you to use alternatives or contact us regarding permission. Here are our full terms for republication. You must credit the author, link to the original story, and name GIJN as the first publisher. For any queries or to send us a courtesy republication note, write to hello@gijn.org.

Read Next

የናይጄሪያው ዓለማቀፍ የምርመራ ዘገባ ማእከል (ICIR) በኮቪድ 19 ምላሽ ተጠሪነትን ለመፍጠር እያደረገ ያለው ግፊት

መቀመጫውን በናይጄሪያ ያደረገ ለትርፍ ያተቋቋመው የናይጄሪያ ዓለማቀፍ የምርመራ ዘገባ ማእከል (ICIR)፣ አሁን ላይ ሽፋኑንም አገሪቱ ለኮቪድ 19 እየሰጠች ባለችው ምላሾች ዙሪያ አድርጓል። በዓለማቀፍ የምርመራ ዘገባ ኔትወርክ (GIJN) የአፍሪካ ኤዲተር ከሆነው ከቤኖን ኸርበርት ኦሉካ ጋር ቆይታ ያደረገው ዳዮ አይታን ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ እንዲሁም ለአፍሪካ ስጋት በሆነው ወረርሽኙ ዙሪያ የምርመር ዘገባ መሥራትን በሚመለከት አንስቷል። ዳዮ አይታን የምርመራ ዘጋቢ፣ የዜና ክፍል አማካሪና የሚድያ አሠልጣኝ ነው።