የደቡብ ሱዳንን ግጭት ለመመርመር የሞባይል ዳሰሳ ጥናት መጠቀም
Read this article in
የደቡብ ሱዳኑ ሚሊየነር ጆሴፍ ዋኒ የገነባው ሁሉ፣ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ እንዳልነበር ሆነ። ሆቴልና ዐስር መደብሮች ወደሙ። ተዘረፉ፣ ተቃጠሉበት። ከወራት በኋላ፣ ይህ ሰው በጎረቤት አገር ኡጋንዳ ስደተኛ ሆኖ በተከራያት አንዲት ትንሽ ቤት ውስጥ እየኖረ ታሪኩን ሲናገር፣ ያንን ያደረጉት የመንግሥት ወታደሮች እንደነበሩም ነገረን። ሕንጻዎች ውስጥ ጎማዎችን አድርገው ያቃጥላሉ፣ ያነዱታል፣ በተመሳሳይ ባለሥልጣናት ያርፉበት የነበረውን ሆቴል በእሳት አጋይተዉታል።
ቡድናችን በደቡብ ሱዳን ያለውን ማፈናቀል፣ የንብረት መነጠቅና ውድመት በሚመለከት ዘገባዎችን እየሠራ ነበር። ደቡብ ሱዳን ከሱዳን ነጻነቷን አግኝታ በ2011 የተመሠረተች አዲስ አገር ነበረች። ለወራት የመሬት ወረራዎች እንደነበሩ ስንሰማ ነበር። አንዳንድ የሥራ ባልደረባዎቻችንም ይህን እውነት በቅርበት መታዘብ ችለዋል። ሆኖም ለዚህ ተጠያቂው ማን ነው እና እንዴት እንዲህ ተስፋፋ የሚለውን ለማወቅ ፈለግን።
ይህን ሳንዘነጋ፣ በ2017 ከሥራ ባልደረባዬና በስደት ላይ ሆኖ የሚሠራው የደቡብ ሱዳን ጋዜጠኛ ከሆነው ላጉ ጆሴፍ ጃክሰን ጋር፣ በአገሪቱ ዙሪያ ያሉ ሰዎችን ለማግኘት እንዲያስችለን የሞባይል ዳሰሳ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል ንድፍ ሠርቻለሁ። የዚህ ግብ የነበረው መንግሥት በጣለው እግድ ምክንያት ልናገኝ ያልቻልናቸውን፣ ያልተማሩና በድህነት ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለማግኘት ነው። ከዛም ነው ‹ፎርስድ አውት› የተሰኘው ፕሮጀክት የተወለደው።
ልትሄዱ በማትችሉባቸው ስፍራዎች ዙሪያ መዘገብ
በደቡብ ሱዳን መገናኛ ብዙኀን ከተፈረካከሰ ቆይቷል። ጋዜጠኞችም በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነውን የእርስ በእርስ ግጭት በሚመለከት ያለውን እውነት ይፋ በማድረጋቸው ዛቻና ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል፣ ሳንሱር ተደርገዋል፣ ታስረዋል፣ አንዳንዶችም ተገድለዋል። በርካታ የውጭ አገራት ጋዜጠኞች፣ እኔን ጨምሮ፣ የመንግሥትን ብሔራዊ ድኅንነት ባለሥልጣናት የሚያስቆጣ ዘገባ በመጻፋችን፣ እውቅና ስንከለከል ወደ አገሪቱ ለመግባትም የፈቃድ ክልከላ ተደርጎብናል።
አሁንም በውስጥ ሆነው እየሠሩ ላሉ ጋዜጠኞች፣ በግጭቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ተደራሽ ለማድረግ ከባድ፣ ውድ እና ብዙ ጊዜ የሚጠይቅ ነው። በዚህም አገሪቱ በዓለም የፕሬስ ነጻነት ዝርዝር ውስጥ ከተካተቱ 180 አገራት ውስጥ፣ ከፓለስታይን እና ማይናማር መካከል 138ኛ ደረጃን ይዛ ትገኛለች።
በርካታ ደቡብ ሱዳናውያን ከቤታቸው ተፈናቅለው በመጠለያ ይገኛሉ ወይም በድንበሮች አቋርጠው ወደ ሌላ አገራት ለመውጣት አስበዋል። ብዙዎቹም ስማርት ስልክ የሌላቸው በመሆኑ፣ በሶርያና በሱዳን በነበሩ አለመረጋጋቶች ይደረግ እንደነበረው፣ የሚፈጸሙ በደሎችን ለመሰነድ አይችሉም። ያንን ማድረግ ቢችሉ እንኳ፣ ብዙ ደቡብ ሱዳናውያን መረጃው እጃችን ላይ ቢገኝስ የሚለውን ስለሚያሳስባቸው ይፈራሉ። ግን ሁሉም ማለት ይቻላል፣ ስማርት ስልክ አይሁን እንጂ ተንቀሳቃሽ ስልክ አላቸው።
ለዚህ ነው፣ ለእኛና እንደ እኛ አመጽ በተንሰራፋባቸው አካባቢዎች ለሚሠሩ ጋዜጠኞች፣ የሕዝብን ድምጽ ለመሰብሰብ ስልክ መፍትሄ የሚሆነው። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ላይ የሚሠሩ ጋዜጠኞች፣ ምንጮቻቸው በለይቶ ማቆያ ካሉ እንዲሁም በእንቅስቃሴ ገደብ ምክንያት በአካል ለመሄድ የማይቻልባቸው ቦታዎች ላይ ለመሥራት ተመሳሳይ መንገድ ሊጠቀሙ ይችላሉ። ቀጥሎም የተዘረዘሩት ነጥቦች በፕሮጀክቱ ሂደት የተማርናቸው ናቸው። እነዚህም ለመድረስ ከባድ በሆኑ አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎችን ለማግኘት ለምርመራ ጋዜጠኞች ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።
በስድስት ቋንቋዎች የስልክ ዳሰሳ ጥናት
ጥናታችን አስቀድሞ የተቀዳው በስድስት ቋንቋዎች ነው። እነዚህም ኢንግሊዘኛ፣ አረብኛ፣ ዳኒካ፣ ኑዌር፣ ባሪ እና ማዲ የሚባሉ ናቸው። መላሾች ስልካቸው ላይ ያሉ ቁልፎችን በመጫን አንዳንዴም መልዕክቶችን በድምጽ በመቅዳት መልስ መስጠት ይችላሉ። እኛ የተጠቀምነው የሞባይል ዳሰሳ ጥናት በመደበኛ የጥሪ አገልግሎት በብሔራዊ ኔትወርክ የተሰራጨ ነው። ለሌሎች የዘገባ ፕሮጀክቶች፣ በዚህ መንገድ ሰዎች አስተያየት ለመስጠትና ለመሳተፍ እንዲስማሙ፣ በአንድ ጊዜ ለብዙዎች መልዕክት መላክን ወይም ለተወሰኑ ዝረዝሮች መደወልን እንደ አማራጭ መጠቀም ያስችላል።
ለምሳሌ የጤና ባለሞያዎች ዝርዝር ወይም በአንድ የተወሰነ ኢንዱስትሪ የሚሠሩ ሰዎች ስልክ ቁጥር ቢኖር ተመሳሳይ መንገድን ለመጠቀም ያስችላል። እኛም የተጠቀምነው የተቀዳ ድምጽ ዳሰሳ ጥናትን ነው። ይህ የሆነው የተማሩ ሰዎች በብዛት ባለመኖራቸው እንዲሁም በኢንተርኔት ተደራሽነት ውሱንነት የተነሳ ነው። ነገር ግን የተሻለ የሞባይል እና ኔትወርክ ተደራሽነት ባለባቸው አካባቢዎች፣ በድምጽ እንዲሁም በጽሑፍ መልዕክት በኢንተርኔት የታገዘ ጥናት ማድረግ ይቻላል።
አስፈላጊ ትብብር
ፕሮጀክቱ እድገት ሲያሳይ የእኛም ቡድን እያደገ ስለሄዶ፣ እንደ አስፈላጊነቱ አጋሮችን ጨምረናል። የጀመርነው ከፑሊትዘር የቀውስ ጊዜ ዘገባ ማእከል (Pulitzer Center on Crisis Reporting) ባገኘነው ሽልማት ነው፣ ይህም እኔና ጃክሰን ከ‹ቪያሞ› ጋር ሽርክ እንድንሆን አስችሎናል። ቪያሞ በስልክ ኔትወርኮች አገልግሎት የሚሰጥና ድምጽ የሚሰበስብ ኩባንያ ነው። በምንጠቀመው ዘዴ ላይ በዋጋ የማይተመን ምክር ከሚለግሱን የስታቲስቲክስ እና የተለያዩ ባለሞያዎች ጋር ሠርተናል።
ቀጥሎም ትኩረቱን በደኅንነት ላይ ካደረገው ከአፍሪካ ዲፌንስ ሪቪው (ADR) ከተባለ መገናኛ ብዙኀን ጋር ትስስር ፈጠርን። ይህ ተቋም ጋዜጠኞችን ወደ አገሪቱ ይልካል። ይህም እኔና ጃክሰን ከኡጋንዳ ሆነን ዘገባዎችን ስንሠራ፣ በተጓዳኝ በመላ አገሪቱ ያለውን ቀውስ እንድንከታተል ረድቶናል። በርከት ላሉ ወራት ከዘለቀ ጥናት፣ ዘገባና የጥናት ዲዛይን በኋላ፣ አልጀዚራ አሳታሚያችን፣ ዘገባዎች እንዲሁም የገጽ ቅንብርና የመልቲ ሚድያ ቅርጾች ላይ አርትዖት ሰጪ ሆኖ ተቀላቀለን።
አዲስ ዘዴ በመጠቀም በዓለማችን አስቸጋሪ በሆኑ አካባቢዎች ዙሪያ በመሥራታችን፣ መነሻ ይዘነው ከነበረው የገንዘብ እንዲሁም የጊዜ በጀት በላቀ ሁኔታ ማቀድ እንዳለብን ተማርን። የዳሰሳ ጥናት መረጃዎችን ለመሰብሰብም በጣም ከባድ ፈተናን ተጋፍጠናል። በጥናቱ መኻል የሚያቋርጡ እንዲሁም በጣም በፍጥነት ስልካቸውን ዘግተው ምላሽ የሚያቆሙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነበር። ይህ አስቀድሞም የጠበቅነው ችግር ቢሆንም፣ ከገመትነው መጠን በላይ ሆኗል።
በተመሳሳይ፣ የአገሪቱ ምጣኔ ሀብት እየወረደ ስለነበር፣ ጥናቱን ለማካሄድ የሚጠይቀን ወጪ እየጨመረ ሄደ። ስለዚህም የናሙና መጠናችንን ለማስፋት እንችል ዘንድ፣ የጥያቄዎችን ቁጥር ለመቀነስ፣ የመመሪያውን ስርዓት ለመቀየር እንዲሁም ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፎችን ለመጠየቅ ተገደናል።
ሀቀኛ ዘዴ
የተጠቀምንበት ዘዴ ያለበትን ውስንነት እና ያንን ዘዴ የመረጥንበትን ምክንያት በሚመለከት ዘገባችን ሀቀኛ መሆኑን ማረጋገጥ ወሳኝ ነጥብ ነበር። ይህን ማድረጋችን አንድን መረጃ ማብራራት በምንጀምርበት ጊዜ፣ ትንታኔአችን እንከኖቻችንን በተሳሳተ መንገድ እንዳያስተላልፉ እርግጠኛ ለመሆን ጠቃሚ አካሄድ ነው። ሁልጊዜም መረጃዎቻችንን ከተለያዩ ዘገባዎች፣ ቃለመጠይቆች፣ የሕዝብ የመረጃ መዝገቦች እንዲሁም ከተባበሩት መንግሥታት ወይም የሂውማን ራይትስ-ዎች እና ከሳተላይት ምስል ላይ የተመሠረቱ ጥናቶች ጋር ለማስተሳሰርና ለማነጻጸር በእነርሱም ለመደገፍ ጥረት እናደርጋለን።
የቁጥር መረጃዎችን ከፍተኛ ትርጉም እንደሚሰጡ አድርገን ላለመያዝ ወስነናል። ይህም የሆነው የደቡብ ሱዳንን የሕዝብ አወቃቀር እንዲሁም መላሾቻችን የሆኑ ወንዶች ወጣቶችና በከተማ የተሻለ ኔትወርክ ሽፋን የሚገኝበት ቦታ ያሉ፣ የተለያዩ መሆናቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው። እነዚህን ውሳኔዎችና ድክመቶቻችንም በሥልት እቅዳችን ላይ በግልጽ አስቀምጠናል። ያንንም ያደረግነው ሰዎች ያንን በመረዳት ውስጥ ሆነው እንዲያነብቡ ነው።
ከ35 ሺሕ በላይ ስልኮች ላይ በመደበኛ የስልክ ጥሪ አገልግሎት እንደደወልንና፣ ከዛም ውጥም ከ2900 በላይ ሰዎች መመሪያውን ሰምተው ቋንቋ እንደመረጡ ለአንባቢዎች ነገርን። 405 ሰዎች በጥናቱ ያሉትን 14 ጥያቄዎች በሙሉ መልሰዋል። እነዚህ ጥያቄዎች ከደቡብ ሱዳን የመሬት ይዞታ መብት ባለሞያዎችና የስታትስቲክስ ባለሞያዎች ጋር በምክክር የተዘጋጁ ናቸው።
ታድያ ምላሽ ከሰጡ 405 ሰዎች ውስጥ፣ አርባ በመቶ የሚሆኑት ከመሬታቸው በግድ እንዲነሱ እንደተደረጉ ወይም ከታኅሳስ 2013 ጀምሮ ከቤታቸው እንዲወጡ እንደተደረጉ ሲናገሩ፣ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ለዚህ የመንግሥት ወታደሮችን ተጠያቂ አድርገዋል።
ማረጋገጫና እና የምንጭ ደኅንነት
ሌላው ትምህርት ባለው አቅም ሁሉ ለተገኘው መረጃ ማረጋገጫ መስጠትና በበርካታ ዘገባዎችና የምርምር ዘዴዎች ማጠንከር ነው። ይህም በከፍተኛ ሁኔታ ጥንቃቄ ለሚፈልጉ ፕሮጀክቶች በተለየ ጠቃሚ ነው።
ጉዳት የደረሰባቸው ንብረቶችን ፎቶዎችን አሰባስበን፣ አውነት መሆናቸውን ለማረጋገጥ ግልጽ የምንጭ ማጣራት ዘዴን (open source investigative techniques) ተጠቀምን። ከምንጮቻችን ሞባይል ስልኮች የተገኙ ፎቶዎች መሆናቸውን ለማረጋገጥም ‹ሜታ-ዳታ›ን ተጠቅመናል። የተቀበልናቸውን ፎቶዎች ከሳተላይት ምስሎች ጋር አነጻጽረን፣ በዛም ከቃለመጠይቆቻችን ከተገለጸልን ጋር የሚመሳሰል የደረሱ ጥፋቶችን ምልክቶች ዐይተናል።
መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥን በመጠቀም ስለደረሱ ውድመቶች ያገኘነውን የቁጥር መረጃ አረጋገጥን። ለምሳሌ ሰዎችን የአንድ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤትን ሥም ጠይቀን፣ ሳተላይት ላይም ምስሉን በመመልከት፣ ከነገሩን በተጓዳኝ የውድመቱን ምስል በማየት የምስል ማስረጃ ለማየት ነው። በሁሉ ማለት ይቻላል፣ በሁሉም ጉዳይ፣ ማስረጃዎች ተመሳሳይ ሆነ። ሰፊ የሆነ ተያያዥ ውድመትም በመላው አገሪቱ፣ በገጠር እንዲሁም አነስተኛ ከተሞች ተመለከትን።
የምንጮች ጥበቃና ደኅንነትን በሂደቱ ሁሉ ከግምት ውስጥ አስገብተናል። መንግሥት ምርመራችን ጣልቃ ለመግባት እንዲሁም የሚሰጡንን ምላሾች ለመስማት ምን ያህል ችሎታ ያለው እንደሆነ እርግጠኛ አልነበርንም። ያንን ለማካካስም፣ መግቢያችን ላይ ተጨማሪ ነጥቦችን ከማስቀመጣችን በተጓዳኝ፣ መላሾች በማንኛውም ሰዓት ስልኩን ሊዘጉ እንደሚችሉ አሳውቀናል። የእኔን ሥም በመግቢያችን ላይ ላለማስተዋወቅም ተስማምተናል፣ ይህንን ያደረግነው ምንጮች ከታገደ ጋዜጠኛ ጋር ግንኙነት አላቸው እንዳይባሉ ለመጠበቅ ነው።
የመንግሥት የክትትል አቅም የት ይደርሳል የሚለውንም ተመልክተናል። በዛም መሠረት የዳሰሳ ጥናቱን ከደቡብ ሱዳን ወደ ስደተኛ መጠለያ ካምፖች እስከማዞር የሚደርስ አማራጭ ይዘን ነበር፣ ነገር ግን ያንን ማድረግ አስፈላጊ ሳይሆን ቀርቷል።
በመጀመሪያ ቪያሞ ሊፈታቸው የሚገቡ አንዳንድ ቴክኒካዊ መሰናክሎች ነበሩ። በተለይም በመጀመሪያ ሰሞን በነበሩ አንዳንድ ሙከራዎች፣ የአውቶማቲክ ተፈጥሮ ያላቸው የስልክ ጠለፋዎች ነበሩ። እነዚህም ጠቃሚ ምላሽ ያልተገኘባቸው፣ የስልክ ጥሪ ሰዓትን እንዲሁም በጀትን ያባከኑ ነበሩ። ነገሩግን ከመንግሥት ይሁን አይሁን የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ እንድንዘገይ ግን አድርጓል።
አስደሳች ውጤቶች
ሂደቱ ረጅም ነበር፣ በርካታ ክስተቶችም ተስፋ አስቆራጭ ነበሩ። መረጃዎቻችን ትርጉም የሚሰጡ ለመሆን በጣም የሚያንሱ ይሆናሉ ብለን ሰግተን ነበር። በየመሃሉ የተቋረጠው መጠን መሻሻሉን ለማረጋገጥ፣ የዳሰሳ ጥናቱ ላይ ማስተካከያ ስናደርግም ዘግይተናል። ሰዎች ዘገባችንን ይጠራጠሩ ይሆን ብለንም ስጋት ገብቶን ነበር።
ስለዚህም በርከት ያለውን ሳምንት ያሳለፍነው ማስረጃዎችን እና በዳሰሳ የተገኙ መረጃዎችን በማረጋገጥ ነው። በዛም ላይ ዘገባችን አሳማኝ እንዲሆን ማረጋገጥ ፈልገናል። ስለዚህም አብዛኛውን ክፍል ታሪክ በመንገርና በኹነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ምሳሌ በመስጠት አቅርበናል፣ ሁሉም ነገር የቁጥር መረጃ ብቻ እንዳይሆን።
ያም ሁሉ ከፍተኛ ዋጋ ነበረው። ታሪኩ/ዘገባው በአገሪቱ ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች የተዳረሰ ሲሆን፣ ዘገባው በተወሰኑ አካባቢዎች እንደ ተረክ እንሰማ ለነበረው ጉዳይ ቁጥር ለማስቀመጥ አስችሏል። በደቡብ ሱዳናውያን ማኅበረሰብ ዙሪያ የመሬት መብትና የሰላም ስምምነት ጉዳዮች ወደ የውይይት አጀንዳ እንዲሆኑም ዘገባው መርቷል። እንዲሁም ፊሊፕ ሜየር የምርመራ ዘጋቦዎችና ኤዲተሮች ሽልማት በተሰኘ ሽልማት፣ በጋዜጠኝነት በምርጥና ተግባራዊ ዘዴ አጠቃቀም ሦስተኛ ደረጃ አሸናፊ ሆኗል።
ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ እንዲሁም በወረርሽኙ ወቅት ተመሳሳይ ፈተና ውስጥ የሚገኙ አገራትም እኛ የተጠቀምነውን ዘዴ ሊጠቀሙ ይችላሉ። ሰዎች በነጻነት በማይንቀሳቀሱባቸው፣ ባለሥልጣናት መረጃዎችን በሚያግዱባቸው፣ ነገር ግን አሁንም ለመሰማት እየጠበቁ ያሉ ብዙ ሰዎች ባሉበት አገራት ማለት ነው።
ካሮላይን ቶምሰን ከኬንያ ናይሮቢ ጋዜጠኛ ናት። በዋናነት በመፈናቀል፣ በሰብአዊ መብት፣ በምጣኔ ሀብትና ፖለቲካ ዙሪያ ዘገባዎችን ትሠራለች። ሥራዎቿ በአልጀዚራ፣ በካናዳ ብሮድካስት ኮርፖሬሽ፣ በፍራንስ 24 እንዱሁም በዋሺንግተን ፖስትና በሌሎችም ቀርበዋል።