Accessibility Settings

color options

monochrome muted color dark

reading tools

isolation ruler

ሪፖርት ማድረግ

Topics

የኮቪድ 19፡ የምርመራ ዘገባ አንጻሮችን በሚመለከት የባለሞያዎች ምክረ ሐሳብ

Read this article in

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቋቋም በሚሰጥ ግብረ መልስ በሚወሰድ ከተለመደው ለየት ያለ እርምጃ ጋር በተገናኘ፣ የምርመራ ጋዜጠኞች ሥልጣንን ያለአግባብ መጠቀምና የተጋላጮችን ብዝበዛ የማጋለጥ ሥራቸው ከዚህ በላይ አስፈላጊ ሆኖ አያውቅም። በፍጥነት እየተከሰተ ያለውን ቀውስ ተከትሎ፣ የምርመራ ጋዜጠኞች ትኩረታቸውን ምን ላይ ማድረግ አለባቸው? እንዲሁም ምን ዓይነት መሣሪያዎችን እና ዘዴዎችን መጠቀም ነው ለኮቪድ 19 ምርመራ ዘገባ ወሳኝ የሚሆነው?

የዓለማቀፍ የምርመራ ዘገባ ኔትወርክ በዓለማቀፍ ማኅበረሰብ መሪ የሆኑ ጋዜጠኞችን ጨምሮ፣ የመረጃ ስህተት፣ የአቅርቦት ሰንሰለትና የግልጽ ምንጭ መሣሪያ ምርመራ ባለሞያዎችን ጠይቆ ነበር፣። ጥያቄውም ጋዜጠኞች በወረርሽኝ ጊዜ ምንን አጥቭቀው መመርመር ይገባቸዋል የሚል ነው። እነርሱም ተከታዩን ነግረውናል፤

ሚራንዳ ፓትሩሲስ
ምክትል ዋና አዘጋጅ፣ በመካከለኛው እስያ እና የክልል ዘገባዎች፣ የተቀናጀ ወንጀል እና የሙስና ዘገባ ፕሮጀክቶች

የገንዘብ ማሸሽ እና የወንጀል እንቅስቃሴዎች ዙሪያ ባለሞያ ነው። መቀመጫውን ሳራጄቮ ያደረገው ፓትሩሲስ፣ የናይት ዓለማቀፍ የጋዜጠኝነት ሽልማት (Knight International Journalism Award) የግሎባል ሻይኒንግ ላይት ኦርጋናይዝ ሽልማት፣ የአይአርኢ ሽልማት እንዲሁም የአውሮፓ ፕሬስ ሽልማት አሸናፊ ነው

በዓለም ዙሪያ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በታወጀበት፣ መንግሥታትም ቫይረሱን ለመቋቋም በሚታገሉበት ጊዜ፣ ያለአግባብ ማትረፍ ለሚፈልጉ አዳዲስ ‹እድሎች› ይፈጠራሉ። በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወረርሽኙን ለመቋቋም በሚል ለአስቸኳይ ግዢዎችና ግልጽ ላልሆኑ ወጪዎች ታቅደዋል። ነገር ግን ይኸው ቀውስ በሥልጣን ላይ ያሉትን ተጠያቂ ለማድረግ አዲስ መንገድ ሰጥቷል። ዘጋቢዎችም የመንግሥትን ወጪዎች መመልከት፣ አዳዲስ ምርት አቅራቢዎችን መለየት፣ ምንጫቸውንና ዋጋቸውን መመልከት አለባቸው።

የተለዩ ምልክቶችን መፈለግ አለብን። እነዚህም ለምሳሌ የሕክምና ምርቶች ግብይት ውስጥ ገብተው የማያውቁ ኩባንያዎች፣ ገለል ባለ መዋቅር የተያዙ ኩባንያዎች፣ ከምሁራን ጋር ባላቸው ግንኙነት የተመረጡ ተጫራቾች፣ በቀደሙ ዓመታት ምንም ያላተረፉ ወይም ጥቂት ያተረፉ ኩባንያዎችና የመሳሰሉት ናቸው። ከመንግሥት መረጃ ማግኘት ከባድ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ ከተወዳዳሪዎችና ቸል ከተባሉት ጋር ማውራት ለምርመራችን የትኩረት አቅጫ ለማግኘት ይረዳናል። ነገር ግን ቀውሱ ቢያቆም እንኳ ሥራችን አያቆምም። በቀጣይ ዓመት የሂሳብ ቋቶች ሲሞሉ፣ ያኔ ያለአግባብ አትራፊነትን በሚገባ መረዳት እንችላለን።

ማላቺ ብሮውኒ
በኒውዮርክ ታይምስ የምስል ምርመራ ከፍተኛ ፕሮድዩሰር

ብሮውኒ እና የእርሱ ቡድን የተለመደውን አዘጋገብ ከዘመናዊ ዲጂታል ወንጀል ምርመራ ጋር በማስተሳሰር፣ ቀዳሚ ሆነዋል። ይህም ከቪድዮዎች፣ ከፎቶ እንዲሁም የድምጽ ቅጂዎች መረጃ በመሰብሰብ፣ ከሳተላይት የተገኙ ምስሎችን መተንተን እና ወንጀል የተፈጸመባቸውን ስፍራዎች በ3-ዲ ዳግም መገንባትን ያካትታል።

የኮሮና ቫይረስ ተጽእኖ ዓለምን ያዳረሰ ነው። ከዛም ደግሞ የአካልና ማኅበራዊ ርቀት አስፈላጊ በሆነበት ጊዜ፣ ሰዎች ግንኙነታቸው በቴክኖሎጂ እና ማኅበራዊ ሚድያ ሆነ። እናም ችግሩን ጠቅላላ ሕዝብ ሊሰማው እንደቻለ ሁሉ፣ በየእለት ኑሮ ላይ በጉልህ እያየነው ነው። ከእነዚህም ድንበሮች መዘጋታቸውን ተከትሎ የታዩ ምስቅልቅል ያሉ ትዕይንቶች፣ ደማቅ የነበሩ ከተሞች ሰዎችን አጥተው ጭር ማለታቸው፣ በሆስፒታል እና ለይቶ ማቆያ ውስጥ ያለውን ፈታኝ ሁኔታ የሚያሳዩን የጤና ባለሞያዎች፣ እንዲሁም እየሠሩ ያሉት ራስን ለመከላከል በቤት ውስጥ የሚሠራ መከላከያ፣ ሰዎች ግንባር ላይ ሆነው ለሚዋጉ ሰዎች በበረንዳና ከቤታቸው ሆነው በማጨብጨብ ያሳዩት አንድነትና ኅብረት ተጠቃሽ ናቸው። በተጨማሪም ማኅበራዊ ሚድያና ሌሎች የኦንላይን አውዶች፣ በወረርሽኙ የመጀመሪያ ወቅት፣ መንግሥት እንዳይገለጽ ሲከላከል በነበረው ወረርሽኙ ዙሪያ ቻይናውያን መረጃዎችን እንዲያቆዩና እንዲያጋሩ አስችለዋል።

የሳተላይት ምስሎችና የቁጥር መረጃዎች የኮሮና ቫይረስ ተጽእኖዎችን ለመመልከትና ለመከታተል ያስችሉናል። የእገሌ ተብለው ያልተለዩ ሞባይል ስልኮችን በምሥል በመከታተል፣ የትኞቹ አካባቢዎች የአካላዊ ርቀት ውጤታማ መከላከያ መንገድ እንደሆነ ማየት ተችሏል። የአውሮፕላን መከታተያዎችና የተጓዦች መረጃዎች በርቀት ጭምር የሰዎች እንቅስቃሴ መቀነሱን ያሳያሉ። ሳይንሳዊ የሆኑ ተቋማትም የሕዝብ ቁጥር መቀነስን ለክተዋ እንዲሁም ተመልክተዋል። የሳተላይት ምስል እና የመርከብ መከታተያ መሣሪያዎች፣ ምን ያህሉ የሰሜን ኮርያ የጦር መርከቦች፣ በቻይና ዙሪያ ከተንቀሳቀሱ በኋላ፣ ወደመነሻቸው እንደተመለሱና፣ ይህም በምጣኔ ሀብት ላይ ስላለው ተጽእኖ ለማሳየት ረድተውናል።

እነዚህና ሌሎች በርካታ ማሳያዎች እንዲሁም መረጃዎች አሁን እየሆነ ያለውን ለማስረዳት አቅም አላቸው። በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመቆጣጠር የወጡ የተለያዩ ፖሊሲዎችን ውጤታማነት በጥልቀት ለመተንተን ይረዳሉ። አንዳንዴም እንደአየር ንብረት በትዕግስትና በሂደት የውድመት መጠኑን ለመገምገም ያግዛሉ። ከእነዚህ ቀውሶች ውስጥስ የፈጠራ ሥራዎች ሊወጡ እንደሚችሉ ማን ያውቃል!

ኤሊዮት ሂጂንስ
ቤሊንግካት ዋና ዳይሬክተር

ቤሊንግካትን በዓለማችን ቀዳሚ ከሆኑ የግልጽ ምንጭ ምርመራ ማእከላት መካከል አንዱ እንዲሆን ያስቻለ ሰው ነው፣ ሂጂንስ። ቡድኑ በ20 አገራት በነበረው አስተዋጽኦና ድርሻ፣ በሜክሲኮ የአደገኛ እጽ አዘዋዋሪዎችን፣ የሶርያ የጦርነት ወንጀሎችን እንዲሁም ሩስያ የመታችውን የ MH17 አውሮፕላን በሚመለከት አጋልጧል። 

አንድ የታዘብኩት ነገር፣ ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ዘገባዎች ዙሪያ፣ ሚድያን ጨምሮ ከመንግሥት ባለሥልጣናትና ከገዛ የቅርብ ጓደኛና ቤተሰባቸው ከሚያዩዋቸው ብዙና የተለያዩ ሐሳቦች የተነሳ፣ የበለጠ እውነታውን የማጣራት ፍላጎታቸው ጨምሯል። በጥንቃቄ የተሞላ እውነታን የማጣራት ሥራና ማረጋገጫ ማቅረብ ጠቃሚ ነው። ነገር ግን አድማጭና አንባቢን ስለምርመራው ደረጃ በደረዳ እያንዳንዱን ሂደት በማስቃኘት፣ እንዲሳተፉ ማድረግ ይቻላል።

በቅርቡ በትዊተር ገጽ ላይ፣ በብዙዎች የሚታወቁ አንዳንድ ፎቶግራፎችን ለማረጋገጥ ከጀመርኩት ሂደት ጋር በተያያዘ ፖስት አደረኩኝ። የተለያዩ መሣሪያዎችንና ዘዴዎችን ለአዳዲስ አድማጭና ተመልካቾች አብራራሁ። ይህን ተከትሎም አንዳንዶች ተቀላቅለው ምስሎቹን በማጣራትና በማረጋገጥ ተሳተፉ። ብዙዎች ቤት እንዲቀመጡ ግድ በተባሉበት ጊዜ፣ ይህ ሰዎች በኦንላይን ቀጥታ የምርመራ ሥራ ገለጻዎች ላይ እንዲሳተፉ ጥሩ እድል የከፈተ ነበር። ተሳትፎው ለትልቅና በጣም ወሳኝ ለሆነ መግለጫ ላይሆን ይቸላል። ብቻ በምርመራ ሥራ ጉዞአችሁ ሰዎችን አስከትላችሁ ተጓዙ።

ፒተር ክሌን
ግሎባል ሪፖርቲንግ ማእከል መሥራችና ዋና ዳይሬክተር

ክሌን ለትርፍ ያልተቋቋመውን ይህን ዓለማቀፍ የዘገባ ማእከል በቢሪቲሽ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የመሠረተው፣ ዓለማቀፍ ጋዜጠኝነት እንዴት ይተግበር የሚለው ላይ አዲስ ነገር ለመጨመር ነው። በመድኃኒት አቅርቦት እና ወረርሽኙ ዙሪያ የምርመራ ሥራዎችን ከፐብሊክ ብሮድካስት ሰርቪስ እና አሶሽዬትድ ፕሬስ ጋር በተመባበር እየመራ ይገኛል። 

በዓለም ዙሪያ ጋዜጠኝነት ከጤና ባለሞያዎች፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ምግብ አቅራቢና ሌሎች ማኅበረሰብ እንዲንቀሳቀስ ወሳኝ ከሆኑ አካላት በተጓዳኝ፣ ‹ጠቃሚ አገልግሎት› እንደሆነ ታምኗል። ይህንን ድርሻ በቁምነገር በመያዝ ወደ ተባለው ደረጃ ከፍ ማለት አለብን። ይህ የእኛን ተዓማኒነት ሲፈታተን የቆየውን ሐሰተኛ ዜና ለመጋፋት ያለን እድል ነው። እውነት ላይ መሠረት ያደረገ ጋዜጠኝነት እንደዚህ ጊዜ ጠቃሚ ሆኖ አያውቅም፣ ስለዚህ እውነታዎቹን በትክክል እወቁ። እናም ለሕዝብ የምትልኩትን መልዕክት በጥንቃቄ አስቡ።

ከወረርሽኙ የመነጨው አንድ ትልቅ ጉዳይ፣ የሕክምና ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለቱ እንዲህ ላለ ቀውስ እንዳልተዘጋጀ በግልጽ የሚያሳይ ነበር። በርካታ የኅብረተሰብ ጤና ባለሞያዎች ዓለማቀፍ ወረርሽኝ እንደሚከሰትና ስርዓቱን ያጨናንቀዋል እያሉ ለዓመታት ሲያስጠነቅቁ፣ ለምን ነበር ያልተዘጋጀነው?

በሕክምና ግብዓት አቅርቦቶች እያተረፈ ያለው ማን ነው? ይህ አካል የተፈላጊ የሕክምና ግብዓቶችን ስርጭት በማገዝም ሆነ ወደኋላ በማስቀረት ሚናው ምን ነበር? እየጨመረ በመጣ የአእምሮአዊ ንብረት ላይ ባተኮረ ኢንዱስትሪ፣ የአእምሮአዊ ንብረት ድርሻ ምንድን ነው? የሕክምና ግብዓት አቅርቦት ሰንሰለቱ አፈጣጠር ምን ያለ ቢሆን ነው፣ እንዲህ ላሉ በፍላጎት ላይ ለሚፈጠሩ ድንገተኛ ለውጦች መልስ እንዳይሰጥ ያደረገው?

ወንጀለኞች በተለያዩ አሠራሮች ውስጥ ያሉ ክፍተቶችን ያያሉ። ይህ ቀውስ ደግሞ ተጋላጭ መሆናችንን ያመላከተ ነው። አሁን ላይ ያለው የነፍስ ማዳኛ መሣሪያ መሠረታዊ ፍላጊት፣ አስቀድሞ የነበረውን የመንግሥትና የንግድ ላይ ሙስና ያባብሰዋል። እኔ በዓለም ዙሪያ ላሉ ጋዜጠኖች የምመክረው፣ የበፊት ዘገባዎቻቸውን እንዲከተሉና አስቀድሞ በየስርቻው የተደበቁትን እንዲያዩ ነው። በቀደመው ጊዜ በተከሰተ አሳፋሪ ተግባር ውስጥ የተሳተፉ ሙሰኛ ባለሥልጣናት ወይም የንግድ ተቋማት ካሉ፣ አሁን ያላቸው ድርሻ ምንድን ነው? እንደ ኮቪድ 19 ያለ ቀውስ፣ የነበረውን የተዛባ አሠራር ሊያባብሰው ይችላል።

ድምጽ ያላቸውና ሀብታም አገራት ትኩረቱንም ቁሰቁሱንም የማግኘት አዝማሚያቸው ከፍተኛ ነበር። ዝቅተኛ አቅም እንዲሁም ሀብት ያላቸው አገራትስ ቀውሱን እንዴት አየተቋቋሙት ነው? የዓለም አገራት መሪዎችስ ይህን የተዛባ አሠራር ለማስተካከል ምን እየሠሩ ነው?

ሆኖም፣ የዓለማችን የሕክምና መሣሪያዎች የሚመረትባቸው አገራት ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ። በተጨማሪም ለውጪ ገበያ የታሰቡ ምርቶችን ይዘው በማቆየት፣ በዚህ ቀውስ ጊዜ በአገራቸው ሊጠቀሙባቸው ይችላሉ። በዚህም ለምርመራ ምቹ የሆኑ ብዙ አንድምታዎች አሉ።

ጂንክዩንግ ብዩን
በደቡብ ኮርያ በሲሳኢን መሪ የምርመራ ዘጋቢ

ብዩን በኮርያ ተጠቃሽ ከሆነው ሲሳኢን ከተባለ ሳምንታዊ ዜና መጽሔት ጋር ትሠራለች። በአገሯም የኮሮና ቫይረስ ቀውሶችን በመዘገብ ግንባር ቀደም ከሚገኙት ጋር ተሰልፋለች

ኮቪድ 19 እንዴት እና ለምን ተሰራጨ የሚለው በእርግጥ ጠቃሚ ጥያቄ ነው። ነገር ግን የቫይረሱ የስርጭት ፍጥነት ጋዜጠኞች በዚህ ‹ለምን› እና ‹እንዴት› የሚል ጥያቄ ላይ እንዲቆዩ አያደርጋቸውም። የምርመራ ጋዜጠኞች ምክንያቱን ከመተንተን ይልቅ ወደፊትም በሚያመላክቱ ጥያቄዎች ላይ ማተኮር አለባቸው። እርግጥ ነው፣ የምርመራ ጋዜጠኞች የወደፊቱን አዋቂም ሆነ ትንቢት ተናጋሪ አይደሉም። ያም ሆኖ ወደፈት ለማየትና ለመተንበይ ጥረት ማድረግ አለብን።

ወደፊት በምንመለከት ጊዜ፣ እንደ መነሻ ልናየው የሚገባው ሌሎች አገራት በወረርሽኙ ስርጭት የገጠማቸውን ፈተና ነው። ለእኛ እንደመነሻ ልንወስድ የምንችለውና፣ ደቡብ ኮርያ የነበራትን ያህል ከፍተኛ ስርጭት የነበራት ብቸኛዋ አገር ቻይና ነበረች። ነገር ግን ቻይና የወሰደቻቸው እርምጃዎች፣ ማለትም እንደ የከተሞች መዘጋጋት፣ የፕሬስ ነጻነት መፈረካከስ እንዲሁም የእንቅስቃሴ ገደብ፣ እንደ አንድ ዴሞክራሲያዊ አገር፣ ለደቡብ ኮርያ የቀረቡ አማራጮች አልነበሩም።

በቻይና የሚወጣው የኮቪድ 19 መረጃውን ግልጽና ነጻ ነው ብሎ ማመንም ከባድ ነበር። ቢሆንም፣ ቻይና በስኬቶቿ መካከል የተጋፈጠችውን ፈተ በመንግሥት የተያዙ መገናኛ ብዙኀን ከሚያወጧቸውን ታሪኮች በመነሳት በተወሰነ መልኩ ማግኘት እንችል ነበር። ነገር ግን ለዚህ ወረርሽኝ ሽፋን በመስጠት፣ የሰዎች ሕይወት ከአንዱ አገር ወደ ሌላው አገር የተለያየ እንዳልነበር ተረድቻለሁ። የሚገጥሙን ፈተናዎችም በጣም ተመሳሳይ ናቸው።

የምርመራ ሽፋን እያንዳንዱ አገር በኮቪድ 19 የወሰደውን እርምጃ የሚያነጻጽር ትንታኔ ማካተት አለበት። አለበለዚያ ለመሥራት ቀላል አይሆንም። አገራት የሚጋፈጧቸው ፖለቲካዊ፣ ባህላዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ፈተናዎች የተለያዩ ናቸው። ስለዚህ ተመሳሳይ ሥልት የተለያየ ውጤት ሊያመጣ ይችላል። በሆኑ የተወሰኑ አገራት ያሉ ጋዜጠኖች እንዲህ ያለውን ኹኔታ ሊረዱ እንደሚችሉ የታወቀ ቢሆንም፣ አንዳንድ አገራት ያሉ ጋዜጠኞች ግን ይህን ላይረዱ ይችላሉና ፍርዳቸውን መሬት ላይ በማይገን ዘገባ ላይ መሠረት ሊያደርጉ ይችላሉ።

የምርመራ ጋዜጠኞች ለዓለምዐቀፍ ትብብር ትክክለኛ እድል አላቸው። ሲሳኢን፣ እኔ የምሠራበት የዜና መጽሔት፣ አነስተኛ ተቋም ሲሆን በአገር ውስጥ ጉዳዮች ላይ ነበር የበለጠ የምናተኩረው። ነገር ግን በዚህ ወረርሽኝ ሰሞን፣ ባህርማዶ የነበሩንን ዜና የሚያጠናቅሩ ተወካዮችን ተሻምተን ያዝን። እንዲሁም በሌላ አገራት ካሉ የጋዜጠኝነት የውይይት መድረኮች ላይ ሰዎችን በማነጋገር፣ ታሪኮችን መጠየቅና ሰዎች በጽሑፍ አስታዋጽኦ እንደሚያደርጉም መጠየቅ ጀመርን። የዓለም ዐቀፍ የሕክምና ጥናታዊ መጽሔቶችም አበጥረን ከመመልከታችን በተጓዳኝ፣ የኅብረተሰብ ጤና ላይ ለሚሠሩ ባለሞያዎች ጥያቄዎችን ላክን።

እንደ ኮቪድ 19 ያለ ወረርሽኝን በምንጋፈጥ ጊዜ፣ በመንግሥታት፣ በሕክምና ባለሞያዎች እንዲሁም በመገናኛ ብዙኀን መካከል ምን ያህል ዓለማቀፍ ትብብር እንደሚያስፈልግ፣ ምን ዓይነት ትብብር እንደሚያስፈልግ፣ የተለየ የመተባበሪያ መንገድ እንዲሁም ምርጥ የተባሉ ልምዶችን መመልከት አለብን። ዓለማቀፍ ኔትወርክ ያላቸው የምርመራ ጋዜጠኞች ያንን ድርሻ ሊወጡ ይችላሉ።

ፋቢዮላ ቶሬስ
ሳሉድ ኮን ሉፓ መሥራች

ቶሬስ መቀመጫዋን በሊማ ያደረገች፣ የሳሉድ ኮን ሉፓ (ጤና በአጉሊ መነጽር) የተባለ በላቲን አሜሪካ የኅበረተሰብ ጤና እና ጋዜጠኝነትን በማስተሳሰር የሚሠራ የዲጂታል አውድ መሥራችና ዳይሬክተር ናት። በተጨማሪም የምርመራ ሳይት ተብሎ የሚታወቀው የ‹Ojo Público› መሥራች ናት። 

ወረርሽኙን ለመቋቋም በሚደረግ ጥረት፣ በላቲን አሜሪካ የሚገኙ በርካታ አገራት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል። እነዚህ እርምጃዎች፣ የሕዝብ ገንዘብ ከተለመደው መንገድ ውጪ በአዲስ ሕግጋትና መመሪያዎች ወጪ ማድረግን ያካትታሉ። እንዲሁም የድንበር መዘጋት እና የተለያዩ ሕዝብን በግድ እንዳይንቀሳቀስ ለማድረግ ዲዛይን የተደረጉ የሲቪል መብቶችና የትራንስፖርት አገልግሎት እገዳዎችን ይጨምራል።

ይህ ለምርመራ ጋዜጠኝነት ፈታኝና የተወሳሰበ ጊዜ ነው። ከመቼውም ጊዜ በላይ አሁን የዓለም የኅብረተሰብ ጤና በትኩረት ሊታይ ይገባል የሚለውን ማሳየት እንችላለን ብዬም አምናለሁ። የኅብረሰተብ ጤና በተለያዩ ማኅበራዊ ዘርፎች ውስጥ የአጀንዳቸው ክፍል እንዲሁም ከኢኮኖሚና አገር ውስጥ አልፎም ዓለማቀፍ ፖለቲካ ጋር በከፍተኛ ሁኔታ የተሳሰረ ነው። የኅብረሰተብ ጤና ጉዳይ ቋሚ የውይይት ርዕስ መሆን ይገባዋል። ስለጤና የምናስበው ስንታመምና ወረርሽኝ ሲመጣ ከሆነ፣ በጣም አርፍደናል።

በመጀመሪያ እለታዊ የዘገባ ሽፋን ስንሰጥ፣ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን ነገር አለ። ይህም አሁን ላይ ለአድማጭ፣ አንባቢና ተመልካቼ ማብራራት ያለብኝ ጠቃሚው ነገር ምንድን ነው? የሚለው ነው። መርሳት የሌለብንም ጋዜጠኝነት የሕዝብ አገልግሎት መሆኑንና፣ ይህም በተለይ የበለጠ ተጋላጭ ለሆኑና ከፖለቲካና የተቋማት ብዝበዛ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ነው።

ኹለተኛ ራሳችንን መጠየቅ ያለብን፣ በዚህ ወረርሽኝ ስጋት ላይ ያለው ምንድን ነው የሚለውን ነው። ማን ነው ከዚህ ዓለማቀፍ ቀውስ እየተጠቀመ ያለው? የመድኃኒት ኮርፖሬሽኖች፣ የባዮቴክ ኩባንያዎች እና ሌሎች የጤና መጠበቂያ ግብዓቶችን የሚያመርቱ አስቀድሞ ከሚደረግባቸው በላይ ጠንከር ያለ ምርመራ ያስፈልጋቸዋል። ብዙ ጊዜ፣ ንግድ እና የአእምሮአዊ ንብረትን መብትን የሚመሩ ሕጎች፣ ከኅብረተሰብ ጤና እና ሰብአዊ መብት ጥቅም አንጻር በተቃራኒው የሚሄዱ ናቸው።

ይህ ቫይረስ ዓለምን ወደ ለየለት መዘጋጋት እንዲያቀና ግድ ብሏል። እነዚህ ኹነቶች ደግሞ በፊት ከነበረው የበለጠ ድህነት እና የእኩልነት እጦት እየፈጠሩ ነው። ስለዚህም የወረርሽኙን ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተጽእኖዎች መመርመር ወሳኝ ነው።

ይህ ወረርሽኝ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የተሻለ ትብብር ያለበት የምርመራ ጋዜጠኝነት እንደሚያስፈልገን አሳይቶናል። በሳሊድ ኮን ዱፓ፣ መረጃዎችን ግልጽ ለማድረግና የተጣሩ መረጃዎችን ብቻ ይፋ ለማድረግ እንዲሁም አግባብ ያልሆነ የሥልጣን አጠቃቀምን ለመዋጋት እንዲረዳ፣ የምርመራ ዘገባ ፕሮጀክቶችን በላቲን አሜሪካ ዙሪያ ከሚገኙ ጋዜጠኞች ጋር በጋራ እየሠራን ነበር።

ማርታ ሜንዶዛ
ናሽናል ፀሐፊ፣ በአሶሽዬትድ ፕሬስ

መቀመጫዋን ሲልከን ቫሊ ያደረገችው ሜንዶዛ፣ የኹለት ጊዜ የፑሊተዘር አሸናፊ ናት አሸናፊ ያደረጋትም በታይ የባህር ምግብ ዘርፍ የተሠራመሩ 2000 ሰዎችን ከባርነት በማላቀቋ እንዲሁም ‹ No Gun Ri› የኮርያ ጦርነት ጭፍጨፋዎችን በማጋለጧ ነው

እኔ ለሪፖርተሮች የምሰጠው ጠቅለል ያለ ምክር፣ ከቻላችሁ ቡድን ፍጠሩ የሚል ነው። አብራችሁ የምትሠሯቸው የቅርብ የሥራ ባልደረቦች በዚህ አስጨናቂ ጊዜ አብረዋችሁ ሲኖሩ፣ በአንድ ጎን ሥራችሁን ከፍ ሲያደርግ፣ በሌላ ወገን በዚህ አስጨናቂ ጊዜ  በየእለቱ ከሰዎች ጋር በሚኖራችሁ ተግባቦት ውስጥ ቀልድና ጨዋታን ያመጣል።

ድምጽ ለሌላቸው ድምጽ መሆን ደግሞ የበለጠ ወሳኝ ነው። ቤት አልባ፣ በእስር ያሉ እና የተገለሉ ሕዝቦች ሊደረሱ ይገባል። የመፈለጊያ መሣረያን በሚመለከት፣ በበኩሌ እንደ Import Genius, Panjiva, USASpending, trac.syr.edu, MarineTraffic, PACER እና ሌሎችን ስጠቀም ነበር።

የአቅርቦት ትስስርን መተንተንን በሚመለከት፣ ግነቱን ትታችሁ ያገኛችሁትን መረጃን ተጠቀሙ። ለመነሻ የተናገራችኋቸው ታሪኮች አንድ ታሪክ እንደሆኑ ይቆዩ፣ ማጠቃለያችሁን በሌላ በምንም ሳይሆን በተገኙ የቁጥር መረጃዎች ላይ አድርጉ። ይህ ዓለማቀፍ ታሪክ ነው፣ ስለዚህ ያንን ወደ ራሳችሁ አቅርቡና ተላመዱት። ነገር  ግን ትልቁን አውድ አትዘንጉ። ጓደኞቼ፣ እንደ ሁልጊዜው፣ ለመረጃ ነጻነት እንቅስቃሴ እናመልክት።

ናታሊያ አንቴሌቫ
ኮዳ ስቶሪ ዋና አዘጋጅ

ቀድሞ የቢቢሲ ኮረስፖንደንት የነበረችው አንቴላቫ፣ የኮዳ ስቶሪ መሥራች ናት። ይህም ቀዳሚና ለትርፍ ያልተቋቋመ እንደ የሳይንስ ጦርነት፣ የተሳሳተ መረጃ፣ የግብረሶዶማውያን ስጋት እንዲሁም ስደት ያሉ የተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በጥልቀት የሚመለከት ነው።

እኔ በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ የምርመራ ዘገባ ለሚሠሩ ጋዜጠኞች የምሰጠው ምክር፣ ጉዳዮን እንደማንኛውም የምርመራ ዘገባ እንዲመለከቱት ነው። ብሩን መከተልና የሰዎችን ታሪክ መንገር። የተሳሳተ መረጃ ማቀበል ተጽእኖ ያደርጋል፣ ምክንያቱም ጉዳዮ ማኅበረሰቡን እየቀየረው ነው። እንደማንኛውም ቀወስ፣ ተጠቂዎችና በአንጻሩ ወንጀለኞች አሉ። የእኛ ሥራ እነርሱን መፈለግ ነው። የትኛው ነው የበለጠ ትንታኔ የሚፈልገው? ኳረንቲን የአእምሮ ጤናችን ላይ ምን እያደረሰ ነው፣ ኮቪድ 19ስ በብቻነት ላይ ምን እያደረገ ነው የሚለውም እንደዛው።

 ይንግ ቻን
ሆንግ ኮንግ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር

ጋዜጠኛና መምህር ይንግ ቻን፣ በሆንግ ኮንግ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና የሚደያ ጥናት ማእከል መሥራች ዳይሬክተር ናት። እየጠፉ ባሉ ዝርያዎች፣ የሰዎች ሕገወጥ ዝውውር እንዲሁም የተደራጁ ወንጀሎችን የተመለከቱ የተደነቁ ምርመራዎችን መርታለች። 

ከጋዜጠኞች ለመጀመር፣ ሪፖርተሮች የቀደመውን ብሂል ‹ገንዘቡን ተከተል› የሚለውን መከተል አለባቸው። ከወረርሽኙ የሕይወትና የሞት ጉዳዮች በስተጀርባ፣ ያለውን የተቋማት ሚና እና የተለየ ፍላጎት በሚመለከት በጥልቀት መርምሩ። ለምሳሌ፣ የምርመራ እና የሕክምና ግብዓት አቅርቦት እጥረት በስተጀርባ ያለው የተቋማት ፍላጎት ምንድን ነው? በአሜሪካ እንዲሁም በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ብዙ ሙከራዎች ይደረጋሉ፣ የትኞቹ የግል ኩባንያዎችና አምራቾች ናቸው ይህን ሙከራ እያደረጉ ያሉት? እነዚህን ቴስቶች ክፍ ለማድረግ እንዳይቻል መሰናክል የሆኑት ምንድን ናቸው?

እንዲሁም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭንብል ጉዳይም አለ። በዓለማቀፍ የአቅርቦት ትስስር፣ የግል፣ የደላላና የተቋማት ፍላጎት ያለው ድርሻ ላይ ያለቀለት እቅድ ያስፈልገናል። ሮይተርስ ይህን በሚመለከት ምርጥ ዘገባ የሠራ ሲሆን፣ ኒውዮርክ ታይምስም በቻይና ስላለው አቅርቦት ዘግቧል። ነገር ግን ይህ የታሪኩ አካል ብቻ ነው።

የመከላከያ ቁሳቁሶችን በሚመለከት፣ የአሜሪካ መገናኛ ብዙኀን ስለመጀመሪያው በመጋቢት መጨረሻ አካባቢ ከቻይና በአየር ላይ ስለተጠለፈው ምርት ዘግቧል። ቀጥሎ በነበረ መግለጫ፣ ምርቶቹ ወደ ግል ገበያ እንደተላኩ አንድ የአሜሪካ ባለሥልጣን ተናገሩ። ‹ጤናማ ያልሆኑ ባህሪዎች ነበሩ› ሲሉም አምነዋል። እንዲህ ያሉ ባህሪዎች ምንድን ናቸው? ጋዜጠኞች በየእለት ለሚወጡ ለውጦች ምላሽ ሲሰጡ ቆይተዋል። ነጥቦችን ማገናኘት እና ግልጽ የሆነውን የስርዓቱን ውድቀት መመርመር አለብን።

ሱዛን ኮምሬ
በደቡብ አፍሪካ በአማቡሁንጋኔ (AmaBhungane) የምርመራ ጋዜጠኛ

ኮምሬ ‹amaBhungane› በተባለ በደቡብ አፍሪካ በሚገኝ ለትርፍ ያልተቋቋመ የምርመራ ዜና ክፍል ውስጥ ትሠራለች። በቡድኑ የጉብታሊክ ፕሮጀክት ውስጥ ትልቅ ድርሻ ነበራት። በዚህም በደቡብ አፍሪካ በዘመኑ ከፍተኛ የተባለውን ሙስና የተጋለጠ ሲሆን፣ በሳንላም የአፍሪካ የፋይናንስ ጋዜጠኛ ተብላም ተሰይማለች። 

የድንገተኛ ጊዜ ግዢዎች፣ ለሙስና፣ ያለአግባብ ለሚያተርፉና ብዝበዛ ለሚያደርጉ በር ከፋች ናቸው። ስለዚህ በበኩሌ ትኩረቴን የማደርገው በዚህ ወቅት በሚደረጉ ድንገተኛ ውሎችና የውል መራዘሞች ነው። በደቡብ አፍሪካ፣ በዋናው የግዢ ቢሮ፣ የውል መራዘሞችና መቋረጦችን በሚመለከት በየሩብ ዓመቱ ያወጣል (እዚህ ላይ ማየት ይቻላል)። ነገር ግን ይህን መረጃ ለማግኘት ከፍተኛ መዘግየት አለ። ስለዚህ ፈጣን ምላሽ ለማግኘት ከውስጥ አዋቂዎች የሚገኙ ጠቃሚ ነጥቦችን ላይ መሠረት ማድረግ አለባችሁ።

በኮሮና ቫይረስ ምክንያት የጎንዮሽ ሆኖ የሚወጣ ለምሳሌ የአካባበቢ ደኅንነት መመሪያ፣ በዚህ ወቅት ለማየት የምንጠብቀው አይደለም። የሕግ ፊርም የሆነው ዌበር ዌንትዜል፣ አንድ ማስታወሻ ነጥብ አውጥቶ ነበር። ከኹለት ሳምንት በፊት በወጣው በዚህ ማስታወሻ፣ በድንገተኛ ክስተቶች የብሔራዊ የአካባቢ አመራር እንዴት እንደሚቀየር ያመላከተ ነበር። ይህም አሁን ገብተን ልንሳተፍበት ያሰብነው ነው። ስለዚህ በአካባቢያዊ ስጋቶች ዙሪያ፣ በኮቪድ 19 ሥም ማረጋገጫ የተሰጣቸውን እከታተላሁ። ነገር ግን አፈጻጸሙ ሁሉ በወረርሽኙ ተጠምዶ ባለበት ጊዜ፣ ሌላስ ምን እየተፈጠረ ነው የሚለውንም ማየት እንደዛው።

ሰይድ ናዛካት
በሕንድ የዳታሊድስ መሥራችና ዋና አዘጋጅ

ናዛካት የመረጃ ጋዜጠኝነት አነሳሽ የሆነውን ‹ዳታ ሊድስ› ያስተዳድራል። ይህም ሥልጠና የሚሰጥና በሕንድ የመጀመሪያውን የቁጥር መረጃ ላይ መሠረት ያደረገ የጤና ጉዳዮች ላይ ዘገባ የሚሠራ ድረገጽንም ይመራል። የ‹ዘ ዊክ› ተወካይ እንደመሆኑም፣ በህንድ ‹prestigious Ramnath Goenk› የተባለ የጋዜጠኝነት ልኅቀት ሽልማት አሸናፊ ሆኗል

እለታዊ ዜናዎች ያለማቋረጥ እየፈሰሱ ባሉበት በዚህ ጊዜ፣ ጋዜጠኞች በብዙ ግፊቶች መካከል ናቸው። ለምርመራ ጋዜጠኞች ግን ወሳኝ ነገር፣ ሐሳባቸውን መሰብሰባቸው ነው። በእለታዊ ክዋኔዎችና መግለጫዎች አትዘናጉ። በጥልቀት ቆፍሩ፣ መርምሩ።

አሁን ላይ ብዙ መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል። ያ መረጃ ስለተከሰተው ቀውስ ምን ይነግረናል? የሕዝብ ሪከርዶች፣ ሰነዶች፣ የመንግሥት የግዢ ትዕዛዞች እና የሕክምና ግብዓት ምርት አቅርቦትን በሚመለከት የኦዲት ሪፖርቶች ምን ይነግሩናል? የባለሥልጣናት ቸልተኝነት የታዩባቸው ጉዳዮች አሉ?

የምርመራ ጋዜጠኝነት የሚጀምረው ታድያ ጥያቄዎችን በመጠየቅና ለጥያቄዎቹ መልስ የሚሰጡ መላሾችን ከማግኘት ነው። ወደ ቱሎች የመጣን እንደሆነ፣ የተለያዩ እንደ InVIDYouTube, DataViewerYandexCrowdTangle ያሉ ኦንላይን መተግበሪያዎችን በመጠቀም የምናገኛቸው ነገሮች ሁሉ እውነትን ለማጣራት ወሳኝ ናቸው። በተጨማሪም ሪቨርስ የምስል ፍለጋ እንዲሁም የሚያሳስቱና ብዙዎች የተቀባበሏቸውን መረጃዎች ለመጣራት የሚያገለግሉ የድምጽ ማረጋገጫ መተግበሪያዎች በዚሁ ይካተታሉ። ሁሌም ማስታወስ ያለብን፣ ያለ በቂ መረጃ፣ እውነት አይኖረንም።

አንዱና ዋናው ጋዜጠኞች ትኩረት ሊሰጡት የሚገባ ጉዳይ፣ የዓለማቀፍ የዱር እንስሳት ንግድን ነው። ኮቪድ 19 እንዲሁም ብዙ መነሻቸው ከዱር የሆነ በሽታዎች፣ በዚህ የተከሰቱ እንደመሆናቸው ማለት ነው። ባለፉት ዓመታት፣ የዱር እንስሳት ንግድ መጠን፣ በሕጋዊ መንገድ ጭምር የሚደረገው፣ ጨምሯል። በአንጻሩ መጠኑ ምን ያህል ነው እንዲሁም በሰዎች ጤና ላይ ምን ዓይነት ተጽእኖ ያደርጋል የሚለውን በሚመለከት ግልጽ የሆነ ምስል የለንም።

ሙሲኪሉ ማጅድ
የናይጄሪያ ፕሪምየም ታይምስ ዋና አዘጋጅ

በናይጄሪያ የምርመራ ጋዜጠኞች ቀዳሚ ከሚባሉት ውስጥ የሚገኘው ሞጅግ፣ በሙስና፣ ሰብአዊ መብት እንዲሁም የሰዎች ሕገወጥ ዝውውር ዘገባዎችን ሠርቷል። ካገኛቸው ሽልማቶች መካከል፣ የግሎባል ሻይኒንግ ላይት ሽልማት፣ የዎሌ ሶዪንካ የምርመራ ዘገባ ሽልማት የመረጋ ጋዜጠኝነት ሽልማት ተጠቃሽ ናቸው 

ይህ ጊዜ ዘጋዎች ወረርሽኙን ለመታገል በሚል በየአገራቸው እየታፈሰ የሚወጣውን በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የሚከተሉበት ጊዜ ነው። በናይጀሪያ ለምሳሌ፣ አንድ የግል ዘርፍ ጥምረት 15 ቢሊዮን የናይጄሪያ ናራ (39 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ) ለፌዴራል መንግሥት ድጋፍ አድርጓል። ይህም የአመራር ጥረትን ለማገዝና በቁሳቁስ የተሟሉ ለይቶ ማቆያዎችን ለመገንበት አልፎም በሽታውን ለመዋጋት የሚያስችሉ ጠቃሚ ቁሳቁሶችና መድኃኒቶችን ግዢ ለመፈጸም ነው። ብዙ በግብር የተገኘ ገንዘብ እየተሰበሰበና ወጪ እየተደረገ ነውና፣ አንዳንድ ባለሥልጣናት ራሳቸውን በሕገወጥ መንገድ ሀብታም ለማድረግ ሊያሴሩ ይችላሉ።

በአብዛኞቻችን አገር ይህ ሁኔታ ተመሳሳይ ነው ብዬ አምናለሁ። ዘጋቢዎችም በባለሥልጣናት የሚደረጉ ወጪዎችንና የግዢ ሂደቶችን መከታተል መቀጠል አለባቸው። እንዲህ ባለ የድንገተኛ አደጋ ወቅት፣ ባለሥልጣናት በአግባብ አለመምራት ወይም የሕዝብ ሀብትን ፈንዶችን ሙሉ በሙሉ የመስረቅ አዝማሚያ አላቸው። አንዳንድ አገራትም ፈንዶችን ለምርምር እና ክሊኒካል ሙከራዎችን ለማድረግ እያፈሰሱ ነው። እንዲህ ካሉ ወጪዎች ዓለም እየተረዳች ስላለችው የገንዘብ ዋጋ ለማወቅ እነዚህን ወጪዎች መከታተል ጥሩ ይሆናል። ወረርሽኙ በመጨረሻ የጥናትና ምርምር ሥራ ፈንድ ለሚያገኙ ብቻ አይደለ፣ ምንም ለማያበረክቱት ሰነፍ ፕሮፌሰሮች ባለጸጋ የሚያደርግ ሆኖ እርፍ እንዳይል፣ ዘጋቢዎች ማጣራት አለባቸው።

ዘጋቢዎች በዚህ ወቅት በዓለም ዙሪያ እየታየ ስላለው የሰብአዊ መብት ጥሰቶችም ትኩረት መስጠት አለባቸው። በብዙ አገራት የእንቅስቃሴ ገደብ የተጣለ ሰሆን፣ ባለሥልጣናት ፖሊስ፣ ወታደር ሌሎች የጥበቃ ኤጀንሲዎችን አሰማርተው የቤት ውስጥ መቀመጥ ፖሊሲዎችን ተፈጻሚ እያደረጉ ነው። ታድያ በአንድንድ አገራት ኤጀንሲዎች በከፍተኛ ሁኔታ ለማስከበር ቀናተኛ እየሆኑ፣ የዜጎችን መብት እየተጋፉ እንደሆነ የወጡ ዘገባዎች አሉ። ዘጋቢዎች እነዚህን ጥሰቶች የመሰነድ ኃላፊነት አለባቸው።

ራዋን ዴመን
የአረብ ሪፖርተሮች ምርመራ ጋዜጠኝነት (ARIJ) ዋና ዳይሬክተር፤

መቀመጫዋን ኦማን ያደረገችው ራዋን ዴመን፣ የአረብ ሪፖርተሮች ለምርመራ ጋዜጠኝነት (ARIJ)ን ትመራለች። ይህ ኤአርአይጄ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚሠራ፣ ለትርፍ ያልተቋቋመ የምርመራ ዘገባ ማእከል ነው። ራዋን የፊልም ሠሪ ሆና ኹለት ዓመት የሠራች ሲሆን፣ በዚህም ለአልጀዚራ ሚድየ ኔትወርክና ለሌሎችም የ30 ሰዓታት ዘጋቢ ፊልሞችን ፕሮድዩስ እንዲሁም ዳይሬክት አድርጋለች። 

 ይህ ለ2020 ከፍተኛ የሚባል ታሪክ ሲሆን፣ ለቀጣይ ለሚመጡ በርካታ ዓመታትም እንዲያው ሆኖ የሚዘልቅ ነው። ይህ የጤና ወይም የሳይንስ ታሪክ ብቻ አይደለም። ይህ የማኅበረ-ፖለቲካ-ኢኮኖሚ ታሪክ፣ የሰብአዊ መብት እና የባህል ታሪክ ነው።

የመጀመሪያ ምክሬ፣ በአንድ ስፍር ስትገኙ ያን ታሪክ ሽፋን ለመስጠት ይሁን እንጂ ጤናችሁን አደጋ ላይ በመጣል ‹ታሪክ እንድትሆኑ› አይደለም። የኮቪድ 19 ዘገባዎች በሰፊው ተፈላጊ ስለሚሆኑ፣ የመረጃ ግልጽነት በጣም አስፈላጊ ነው። ጋዜጠኞች ተመሳሳይ ጉዳይ ዙሪያ ሽፋን እየሰጡ ከመሆኑ አንጻር፣ እንዲሁም አብዛኞቹ አገራቸውን ትተው መውጣት ስለማይችሉ፣ ድንር ለሚሻገር ትብብር ምርጥ የሚባል እድል ነው። በተመሳሳይ፣ የእናንተን ታሪክ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው የሚለውን ራሳችሁን መጠየቅ ጠቃሚ ነው። ተለዋዋጭና በፍጥነት የሚቀያየር ሁኔታ እንደመሆኑ፣ ከተለመደው በሼልፎች ለረጅም ጊዜ መቆየት ከሚችለውና የረጅም ጊዜ የምርመራ ዘገባ ሥራ በተጓዳኝ በአጭር ሂደት የሚያልቁ ፈጣን ውጤት የሚያሳዩ የምርመራ ሥራዎች ሊያስፈልጉን ይችላል።

ከቤታቸው ሆነው የምርመራ ዘገባ ሥራን ለሚሠሩና መስክ ወጥ ለመሥራት እድሉ ለሌላቸው ደግሞ፣ ባለሞያዎችን ስታነጋገሩ ባለሞያዎቹ የሚያውቁትን ሳይሆን ያንን እንዴት እንዳወቁ ንገሩን። ሞዴሉን ብቻ ሳይሆን፣ ከሞዴሉ ኋላ ያለውን አነሳሽ ምክንያት፣ ቁጥሮችን ብቻ ሳይሆን አውዳቸውን ሸፍኑ።

የጤና ዘርፍ ላይ ያሉ ባለሥልጣናትና ፖለቲከኞች የሚናገሩትን በጥንቃቄ በመተንተን ተጠያቂ አድርጓቸው። በተጨማሩም የተለያዩ ስልቶችን እና አንዳንድ ዲጂታል የሆኑ መተግበሪያዎችን መጠቀም ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ እንደ Signal, Jitsi ወይም Zoom የመሳሰሉ፣ ከምንጮችን ጋር ለማውራት መጠቀም አስፈላጊ ነው። ይህ ጊዜ አዳዲስ ግንኙነቶችን ከአዳዲስ ምንጮች ጋር የምትመሠርቱበትና በተቻለ መጠን አማራጭ የምታሰፉበት ነው። በመጨረሻም፣ በቫይረሱ የተያዙትን እንዳታገሉ እና በአዘጋገባችሁ ዘረኝነት እንዳይንጸባረቅ ጥንቃቄ አድርጉ።

Republish our articles for free, online or in print, under a Creative Commons license.

Republish this article


Material from GIJN’s website is generally available for republication under a Creative Commons Attribution-NonCommercial 4.0 International license. Images usually are published under a different license, so we advise you to use alternatives or contact us regarding permission. Here are our full terms for republication. You must credit the author, link to the original story, and name GIJN as the first publisher. For any queries or to send us a courtesy republication note, write to hello@gijn.org.

Read Next

የናይጄሪያው ዓለማቀፍ የምርመራ ዘገባ ማእከል (ICIR) በኮቪድ 19 ምላሽ ተጠሪነትን ለመፍጠር እያደረገ ያለው ግፊት

መቀመጫውን በናይጄሪያ ያደረገ ለትርፍ ያተቋቋመው የናይጄሪያ ዓለማቀፍ የምርመራ ዘገባ ማእከል (ICIR)፣ አሁን ላይ ሽፋኑንም አገሪቱ ለኮቪድ 19 እየሰጠች ባለችው ምላሾች ዙሪያ አድርጓል። በዓለማቀፍ የምርመራ ዘገባ ኔትወርክ (GIJN) የአፍሪካ ኤዲተር ከሆነው ከቤኖን ኸርበርት ኦሉካ ጋር ቆይታ ያደረገው ዳዮ አይታን ስለ ቡድኑ እንቅስቃሴ እንዲሁም ለአፍሪካ ስጋት በሆነው ወረርሽኙ ዙሪያ የምርመር ዘገባ መሥራትን በሚመለከት አንስቷል። ዳዮ አይታን የምርመራ ዘጋቢ፣ የዜና ክፍል አማካሪና የሚድያ አሠልጣኝ ነው።